ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ 2025 በመጪው ግንቦት ወር በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤መጋቢት 17/2017 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ዓለም አቀፍ ኤክስፖ 2025 ከመጪው ግንቦት 8 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ቀናት በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ይካሄዳል።

በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እና በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የሚዘጋጀው ኤክስፖ በምስራቅ አፍሪካ ትልቁ የቴክኖሎጂ ሁነት መሆኑ ተገልጿል።

ኤክስፖውን በተመለከተ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ እና የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ እንዳሉት፤ ኤክስፖው ኢትዮጵያ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ያስመዘገበቻቸው ስኬቶችን ለዓለም ለማስተዋወቅ ያለመ ነው።

በኢትዮጵያ የትራንስፎርሜሽን ዲጂታል ኢኮኖሚን በማሳለጥ የበለጸገ ማህበረሰብና ሀገር ለመፍጠር በተከናወኑ ተግባራት አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

የተቀናጀ እና ወጪ ቆጣቢ የዲጂታል ቴክኖሎጂ በመገንባት ሂደት የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ገንቢ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል፡፡

የሳይበር ደህንነት፣አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ፣ የፋይናንስ ደህንነት፣ ስማርት ሲቲ እና የቴክኖሎጂ ትምህርት በኤክስፓው የትኩረት ነጥቦች መሆናቸውን ተናግረዋል።

እነዚህን አምስት የትኩረት መስኮች በአንድ ላይ የያዘ ኤክስፖ በመሆኑ በምስራቅ አፍሪካ ትልቁ የቴክኖሎጂ ሁነት ያደርገዋል ብለዋል።

በኤክስፓው ከ10 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች እንደሚጠበቁ ገልጸው፣ የጎንዮሽ ስብሰባዎች፣ ኤግዚቪሽን፣ ሲምፖዚየም እና ውድድሮች የሚካሄዱበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና በበኩላቸው፣ ኤክስፖው ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂዋን በዓለም የምታስተዋውቅበት፣ እንዲሁም ከዓለም የምትማርበት የቴክኖሎጂ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም የግሉ የቴክኖሎጂ ዘርፍ ተዋንያን በስፋት እንዲሳተፉ በማድረግ በዘርፉ ልምድ የሚለዋወጡበትን አውድ ይፈጠራል ብለዋል።

ኤክስፖው ከአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 የዲጂታላይዜሽን ጉዞ ጋር የተጣጣመ መሆኑን ገልጸው፣ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ውድድር እንደሚደረግም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም