በምስራቅ ሸዋ ዞን በህዝብ ተሳትፎ ከ600 በላይ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ሸዋ ዞን በህዝብ ተሳትፎ ከ600 በላይ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል
አዳማ፤መጋቢት 17/2017 (ኢዜአ፦በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን በህብረተሰቡ ተሳትፎ ከ600 በላይ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ግርማ ለማ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ በዞኑ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል እንዲቻል በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በታችኛው የትምህርት እርከን ላይ ትኩረት ተደርጓል።
በዚህም በኅብረተሰቡ ተሳትፎ በተገኘ 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ወጪ በዞኑ 11 ወረዳዎች ደረጃቸውን የጠበቁ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን አስረድተዋል።
በዚህም በዞኑ ባለፉት አምስት ዓመታት ለቅድመ አንደኛ ትምህርት በተሰጠው ትኩረት ከ600 በላይ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ተማሪዎችን ተቀብለው እያስተማሩ መሆኑን ገልጸው፥ በዚህም 52 ሺህ 590 የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
ለትምህርት ቤቶቹም የንጹህ መጠጥ ውሃ እና በፀሐይ ኃይል የሚሰራ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት በመዘርጋት ለመማር ማስተማሩ ስራ ምቹ መደላድል መፈጠሩን አውሰተዋል።
በቀጣይም በሁሉም የገጠር ቀበሌዎች የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተደራሽ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል ባለፉት አምስት ዓመታት በዞኑ ለሚገኙ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 1 ሺህ 193 ደረጃቸውን የጠበቁ ተጨማሪ የማማሪያ ክፍሎች እና 921 የመምህራን መኖሪያ ቤቶች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን አውስተዋል።
በዞኑ የመቂ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቱሪ አህመድ በበኩላቸው የትምህርት ዘርፉን የማሻሻል ሥራ ለመንግሥት ብቻ የሚተው አይደለም።
ለዚህም የከተማዋን ህዝብ ያሳተፈ የትምህርት ተቋማት ግንባታ፣ የተማሪዎች ምገባና የተለያዩ ሥራዎች ተግባራዊ መደረጋቸውን አመልክተዋል።
እስካሁን ድረስ በከተማዋ በ16 ሚሊዮን ብር ወጪና በህዝብ የቁሳቁስ፣ የጉልበትና የሙያ ተሳትፎ ስድስት ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው 900 ህጻናትን የትምህርት እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የትምህርት ቤቶቹ መገንባት የነዋሪዎችን ጥያቄ የመለሰ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው ትምህርት ቤቶችን ምቹና ሳቢ ለማድረግ በተጀመረው በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ መርሃ ግብርም አበረታች አፈፃጸም መመዝገቡንም አክለዋል።