ጣልያን ከኢትዮጵያ ጋር በቡና ዘርፍ ያላትን ትብብር የማጠናከር ፍላጎት እንዳላት ገለጸች - ኢዜአ አማርኛ
ጣልያን ከኢትዮጵያ ጋር በቡና ዘርፍ ያላትን ትብብር የማጠናከር ፍላጎት እንዳላት ገለጸች
አዲስ አበባ፤መጋቢት 17/2017 (ኢዜአ)፦የጣልያን የልማት ትብብር ኤጀንሲ ከኢትዮጵያ ጋር በቡናው ዘርፍ ያለውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኑን አስታወቀ።
የልማት ኤጀንሲው ከእ.አ.አ 2006 አንስቶ በኢትዮጵያ የቡና ልማት የእሴት ሰንሰለት መፍጠር ላይ እየሰራ ይገኛል።
የኤጀንሲው ዳይሬክተር ሚሼል ሞራና የቡናው ዘርፍ ጣልያን ከኢትዮጵያ ጋር ትብብሯን ማስፋት ከምትፈልግባቸው መስኮች አንዱ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።
ጣልያን የግሉ ዘርፍ በኢትዮጵያ የቡና ልማት ውስጥ ያለው ተሳትፎ እንዲያድግ ድጋፍ ማድረግ እንደምትፈልግ አመልክተዋል።
በዚህም የጣልያን የግሉ ዘርፍ ከሀገር በቀል አምራቾች ጋር በማስተሳሰር ለኢትዮጵያን የቡና ዘርፍ ሙያዊ ድጋፍ የመስጠት ፍላጎት እንዳለም አንስተዋል።
በጣልያን መንግስት ድጋፍ እየየተገበረ የሚገኘው የኢትዮጵያ የቡና ዘርፍ የእሴት ሰንሰለትን የማጠናከር ፕሮጀክት ውጤቶች እየተገኙበት ነው ብለዋል ዳይሬክተሩ።
ለኢትዮጵያ የቡና ዘርፍ እድገት ጣልያን የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል አመልክተዋል።
የሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ትብብር የበለጠ እንዲጠናከር ቁርጠኛ መሆኗንም አክለዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ በቡና ኤክስፖርት ከፍተኛ እምርታ አሳይታለች።
ኢትዮጵያ በ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት ስምንት ወራት ወደ ተለያዩ ሀገራት ከላከችው ቡና ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቷን የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን መረጃ ያመለክታል።
‘
ኢትዮጵያ በተያዘው በጀት ዓመት 400 ሺህ ቶን ቡና በመላክ 2 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት አቅዳለች።