ቀጥታ፡

የዩናይትድ ኪንግደም ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያሉ ምቹ የኢንቨስትመንት እድሎች እንዲጠቀሙ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፤መጋቢት 17/2017 (ኢዜአ)፦የዩናይትድ ኪንግደም ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያሉ ምቹ የኢንቨስትመንት እድሎች በመጠቀም መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ጥሪ አቀረቡ።

የኢትዮ-ዩናይትድ ኪንግደም ኢንቨስትመንት ፎረም በለንደን ተካሄዷል።

በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና ኢኒስቲትዩት ኦፍ ዳይሬክርስ አፍሪካ ግሩፕ የተሰኘ ኩባንያ ፎረሙን በጋራ አዘጋጅተዋል።

ፎረሙ በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት እድሎችን ማስተዋወቅ እና የኢትዮጵያና ዩናይትድ ኪንግደም የኢኮኖሚ ግንኙነትን ማጠናከር አላማ ያደረገ ነው።

በፎረሙ ላይ የንግዱ ዘርፍ ተዋንያን ተገኝተዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በፎረሙ ላይ ተሳትፏል።

አምባሳደር ምስጋኑ በኢትዮጵያ እያደገ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ አስመልክቶ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን የዩናይትድ ኪንግደም ኩባንያዎች በሀገሪቷ ያለውን አቅም እንዲመለከቱ ጥሪ አቅርበዋል።

በፎረሙ ላይ በበይነ መረብ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) ኢትዮዮጵያ ለውጭ ኢንቨስተሮች ይበልጥ ሳቢ እንድትሆን ያደጉትን የሕግ እና የተቋማት ሪፎርሞች በማንሳት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ መለከት ሳህሉ በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት መስክ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው የዩናይትድ ኪንግደም ባለሀብቶች የሚያገኙትን ድጋፍ እና የአጋርነት እድሎች በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።

ካጎል የተሰኘው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኩባንያ አመራሮች እና ተወካዮች ኩባንያ በኢትዮጵያ በመሰማራት ያገኘውን ምቹ ከባቢ አየር እና የገበያ ሁኔታ አስመልክቶ ሀሳባቸውን ለፎረሙ ተሳታፊዎች አካፍለዋል።

በዩናይትድ ኪንግደም እና ሰሜን አየርላንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብሩክ መኮንን የዩናይትድ ኪንግደም ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት እድሎችን እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።

ፎረሙ የኢትዮጵያ እና ዩናይትድ ኪንግደምን የኢኮኖሚ ትብብር የሚያጠናክር እና በኢንቨስትመንት እና በተለያዩ መስኮች ያለውን ትብብር የሚያጎለብት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

ኢኒስቲትዩት ኦፍ ዳይሬክተርስ አፍሪካ ግሩፕ የተሰኘው ኩባንያ በዩናይትድ ኪንግደም እና በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ እና የኢኮኖሚ ትስስር ማጠናከር ላይ የሚሰራ ዓለም አቀፍ ኩባንያ ነው።

ኩባንያው በዓለም የተለያዩ ክፍሎች ከ20 ሺህ በላይ አባላት አሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም