ኢትዮ ቴሌኮም እና ማስተርካርድ የዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎቶችን በጋራ ማሻሻል የሚያስችል ስትራቴጂያዊ ውይይት አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮ ቴሌኮም እና ማስተርካርድ የዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎቶችን በጋራ ማሻሻል የሚያስችል ስትራቴጂያዊ ውይይት አደረጉ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 16/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ እና የማስተርካርድ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ማርክ ኤሊዮት በኢትዮጵያ አዳዲስ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን ለማስጀመር የትብብር እድሎችን መፈተሽ የሚያስችል ውይይት አካሂደዋል።
በውይይቱ የሁለቱ ተቋማት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎችም መሳተፋቸውን ከኢትዮቴሌኮም የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ተቋማቱ የመከሩበት የትብብር ማዕቀፍ የቴሌብርን እና የማስተር ካርድን ፕላትፎርሞች በመጠቀም የዲጂታል ፋይናንስ ሶሉሽኖችን ለማሳደግ፣ የፋይናንስ ተደራሽነትን በከፍተኛ ሁኔታ ለማስፋት እና ዘላቂ እድገትን ለማበረታታት ያለመ መሆኑም ተገልጿል።
የኢትዮቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ተቋማቸው በአፍሪካ ትልቅ የደንበኞች ቁጥር እና ግዙፍ መሠረተ ልማት ያለው በመሆኑ ይህም አዳዲስ እድሎችን ለመክፈት አስቻይ ሁኔታ እንደፈጠረለት አብራርተዋል።
በዚህም ከማስተርካርድ ጋር በአጋርነት ለመስራት ያላቸውን ተነሳሽነት አረጋግጠዋል።
የማስተርካርድ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ማርክ ኤሊዮት በበኩላቸው የኢትዮቴሌኮም ፈጣን የደንበኞች ቁጥር ዕድገት እና ግዙፍ የመሰረተ ልማት አቅም ለአጋርነት ተመራጭ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
ለማስተርካርድም ይህ ትብብር መልካም አጋጣሚ የፈጠረለት መሆኑንና ለተግባራዊነቱ ቁርጠኛ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።
ይህ ስትራቴጂያዊ ትብብር ኢትዮጵያን በዓለም የዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ያላትን ተወዳዳሪነት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድግም በመረጃው ተጠቁሟል።
ይህም ዘላቂ ዕድገትንና የሀብት ፈጠራን በማበረታታት አካታች እና ሁሉን አቀፍ የዲጂታል ፋይናንስ ምህዳር እንዲሁም ዘላቂ እድገት ለማስመዝገብ እንደሚያስችልም ተገልጿል።