ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲያዊ ጥረት እና በሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ለአፍሪካ የጋራ ደህንነት እና ለዓለም ሰላም መረጋገጥ ያላትን ቁርጠኝነት  በተግባር አሳይታለች

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 16/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲያዊ ጥረቷ እና በሰላም ማስከበር ተልዕኮዎቿ ለአፍሪካ የጋራ ደህንነት እና የዓለም ሰላም መረጋገጥ ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር ማሳየቷን አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ገልጸዋል።

በአፍሪካ ህብረት እና በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን(ኢሲኤ) የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ እና ለዓለም ሰላም መከበር ያላትን የጸና መሻት ከቃል ባለፈ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ እና በዲፕሎማሲ ጥረቶቿ በተግባር አሳይታለች ብለዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት አዲስ ተመራጭ አባል ሀገራትን የመቀበል ስነ-ስርዓት ዛሬ በታንዛንያ አሩሻ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

በአምባሳደር ሂሩት ዘመነ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በስነ-ስርዓቱ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።

በመድረኩም አምባሳደር ሂሩት የአፍሪካ ህብረት ኢትዮጵያ የምክር ቤቱ አባል እንድትሆን ለሰጠው ድጋፍ አመስግነዋል።

ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲያዊ ጥረቷ እና በሰላም ማስከበር ተልዕኮዎቿ ለአፍሪካ የጋራ ደህንነት እና የዓለም ሰላም መረጋገጥ ያላትን ቁርጠኝነት እና ድጋፍ በተግባር ማሳየቷን ገልጸዋል።


 

የቀውስ ሁኔታዎች ወደ ግጭቶች እንዳያመሩ የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ ስርዓትን ማጠናከር እንዲሁም የግጭት መከላከያ አማራጮችን በመተግበር ሰላምን ማጽናት እንደሚገባ አመልክተዋል።

አምባሳደር ሂሩት አሁን ካለው አህጉራዊ ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር የምክር ቤቱን የፋይናንስ አቅም ዘላቂነት እና ውጤታማነት በሚያረጋግጥ መልኩ መደገፍ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ የዓለም ተለዋዋጭ የጂኦ ፖለቲካዊ ሁኔታ ውስጥ በአፍሪካ እና በተቀረው ዓለም ላይ የፈጠረውን ነባራዊ እውነታ በውል የተገነዘበ ዝግጅት በማድረግ በአህጉሪቱ የጋራ ፍላጎት ውስጥ ትርጉም ያለው ሚና መጫወት ይኖርበታል ነው ያሉት።

በስነ ስርዓቱ ላይ የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት አዲስ አባላት ኢትዮጵያ እና ኢስዋቲኒ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

በድጋሚ አባል ሆነው የተመረጡት ካሜሮን እና ናይጄሪያም በሁነቱ ላይ ተገኝተዋል።


 

ኢትዮጵያ በምክር ቤቱ በማርች 2025 በታዛቢነት እያገለገለች ሲሆን ከእ.አ.አ አፕሪል ወር 2025 አንስቶ በይፋ በአባልነት ማገልገል እንደምትጀምር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በታንዛንያ አሩሻ የሚካሄደው የአቀባበል እና ልምድ ልውውጥ መርሃ ግበረ እስከ መጋቢት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።

የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት በየካቲት ወር 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ባደረገው 46ኛ መደበኛ ስብሰባ አራት የህብረቱን የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት አባላት መምረጡ ይታወቃል።

በዚህም ኢትዮጵያ ከምስራቅ አፍሪካ፣ ኢስዋቲኒ ከደቡባዊ አፍሪካ፣ ካሜሮን ከማዕከላዊ አፍሪካ እና ናይጄሪያ ከምዕራብ አፍሪካ አባል ሆነው መመረጣቸው የሚታወስ ነው።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት የእ.አ.አ 2025 እስከ 2027 የቆይታ ዘመን አባል ሆና ተመርጣለች።

21 ዓመታትን ያስቆጠረው የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት በአህጉሪቱ ግጭቶች እንዳይከሰቱ አስቀድሞ መከላከል፣ የግጭት አስተዳደርና አፈታት ላይ ከፍተኛ የውሳኔ ሰጪ አካል ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም