ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ የተሻሉ ተሞክሮዎች ያላት ሀገር ናት

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 16/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ የተሻለ ተሞክሮ ሊወሰድባቸው የሚችሉ ስራዎች ማከናወኗን የኢስዋቲኒ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ካንያክዌዝዌ ማቡዛ ገለጹ።

በኢስዋቲኒ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ የተመራ ልዑክ በጤና ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር የልምድ ልውውጥ አድርጓል።

ልዑኩ የተሞክሮ ልውውጥ ያደረገው በኢትዮጵያ የጤና አጠባበቅ ስርዓት በተለይም በመድሃኒትና ህክምና ግብዓት አቅርቦት ሰንሰለት ላይ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የኢስዋቲኒ ልዑክ ከኢትዮጵያ ጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬህይወት አበበ ጋር በኢትዮጵያ የጤና አጠባበቅ ሥርዓቶች ላይ ተወያይቷል።

በዋናነት የመድሃኒትና ህክምና ግብዓት አቅርቦት ስርዓትን ለማሻሻልና ለማዘመን ኢትዮጵያ የጀመረችው መልካም ተሞክሮ የተመለከተ ገለጻ ለልዑኩ ቀርቧል።

የኢስዋቲኒ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ካንያክዌዝዌ ማቡዛ ከኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ የመማር እድል በማግኘታቸው እንደተደሰቱ ገልጸዋል።

በልምድ ልውውጡ ለሀገራቸው የሚጠቅም የጤና ፖሊሲዎችን እና ተሞክሮ ሊሆኑ የሚችሉ ጠቃሚ ግንዛቤዎችን ማግኘታቸውን አመልክተዋል።

በተያያዘም የልዑካን ቡድኑ የኢትዮጵያ የፋርማሲዩቲካል አቅርቦት አገልግሎትንም ጎብኝቷል።

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አቡድልቃድር ገልገሎ ጉብኝቱ የልዑካን ቡድኑ አባላት የኢትዮጵያን የመድኃኒት አቅርቦት አስተዳደር አካሄድ እንዲገነዘብና የመድኃኒቶች ተደራሽነት አማራጮችን ለመረዳት እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እና ኢስዋቲኒ በጤናው ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ከስምምነት ላይ መድረሳቸውንም በመረጃው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም