ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና አልጄሪያ በማዳበሪያ ዘርፍ በትብብር መስራት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ተወያዩ

አዲስ አበባ፤መጋቢት 16/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) የአልጄሪያ የኢነርጂ፣ ማዕድን እና ታዳሽ ኃይል ሚኒስትር መሐመድ አርካብን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ሁለቱ ወገኖች ከተወያዩባቸው ጉዳዮች መካከል ኢትዮጵያ እና አልጄሪያ በማዳበሪያ ምርት ዘርፍ በትብብር ሊሰሩባቸው የሚችኩ ጉዳዮች ይገኙበታል።

የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፍ እና ስርጭት እንዲሁም ከሀገራቱ የጋራ ፍላጎት እና ትብብር የሚጣጣሙ መስኮችን መለየት ላይም መክረዋል። 

በውይይቱ ወቅት ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለው የኢኮኖሚ ሪፎርም ለኢንቨስትመንት ይበልጥ ምቹ ከባቢን መፍጠሩ ተነስቷል። 

ኢትዮጵያ ዘለዓቂ ልማት እና የጋራ የኢኮኖሚ ለውጥን በሚደግፍ መልኩ ከአልጄሪያ ጋር ያላትን አጋርነት ለማጠናከር እንደምትሻ መግለጿን ኢዜአ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

የአልጄሪያ የኢነርጂ፣ ማዕድን እና ታዳሽ ኃይል ሚኒስትር መሐመድ አርካብ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ኢትዮጵያ እንደሚገኙ ይታወቃል።

ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ኢትዮጵያ እና አልጄሪያ በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን ትብብር ማጠናከር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ የሁለትዮሽ ውይይቶችን አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም