በሶማሌ እና አፋር ክልሎች የተገኘውን ሰላም መጠበቅ እና ማጽናት ይገባል -የሰላም ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌ እና አፋር ክልሎች የተገኘውን ሰላም መጠበቅ እና ማጽናት ይገባል -የሰላም ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤መጋቢት 16/2017(ኢዜአ)፦በሶማሌ እና አፋር ክልል የተገኘውን ሰላም መጠበቅ እና ማጽናት እንደሚገባ የሰላም ሚኒስቴር ገለጸ።
የሶማሌና አፋር የወንድማማችነት ግንኙነት ማጠናከሪያ መድረክ በአዲስ አበባ ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር)፥ ከለውጡ ወዲህ በህዝቦች መካከል ያለውን አንድነት ለዘላቂ ሰላም እና ጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ለማዋል እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በሶማሌና አፋር ክልሎች ተፈጥረው የነበሩ ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ በጋራ መግባባት ለመፍታት የተከናወኑ ስራዎች ውጤት ማምጣታቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም የሁለቱን ወንድማማች ህዝቦች አብሮነት አጠናክረው ለሚያስቀጥሉ ተግባራት ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ቸሩጌታ ገነነ በበኩላቸው፥ በሁለቱ ክልሎች መካከል አልፎ አልፎ ያጋጥሙ የነበሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት ዘርፈ ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።
በዚህም ችግር ተከስቶባቸው በነበሩ አካባቢዎች አሁን ላይ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መኖሩን ጠቅሰው፥ ዛሬ የጀመረው የውይይት መድረክም የሁለቱን ህዝቦች ግንኙነት ለማጠናከር መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
የተገኘውን ሰላም መጠበቅ እና ማጽናት እንደሚገባ በማንሳት፤ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የህብረተሰቡን ተሳትፎ ማጎልበት እንደሚገባ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ፥ ችግሮችን ለማከም የጋራ ስራ መስራት እንደሚገባ አንስተዋል።
በሁሉም በኩል ጥፋቶችን በመቀበል ለማስተካከል መወሰንና በአዲስ ምዕራፍ ወደ ፊት መሻገር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ኡዝታዝ በድሩ ሁሴን በበኩላቸው፥ የሰውን ልጅ ክቡርነት ሁልጊዜ ማስታወስ እንደሚገባ በመጠቆም፥ ሁሉም በተሰማራበት መስክ በፈጣሪ የሚወደድ መልካም ስራን ሰርቶ ማለፍ እንዳለበት ጠቁመዋል።
በመድረኩ ከሁለቱ ክልሎች የተውጣጡ ምሁራን፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎችም ተገኝተዋል።