ቀጥታ፡

በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል የበኩላችንን እንወጣለን

አዲስ አበባ፤መጋቢት 16/2017(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል የበኩላቸውን ኃላፊነትን እንደሚወጡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች ኮከስ ሰብሳቢ ወይዘሮ ኪሚያ ጁንዲ ገለፁ።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣የሳይንስና የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) ጋር በመተባበር ያዘጋጁት በሴት ልጅ ግርዛት፣ያለእድሜ ጋብቻና ፆታዊ ጥቃት ላይ ያተኮረ አውደጥናት እየተካሄደ ይገኛል።

አውደጥናቱ ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ላይ የተሰሩ ስራዎች፣ የመጡ ለውጦችና የሚቀሩ ተግባራት ላይ ይመክራል።

በአውደጥናቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች ኮከስ ሰብሳቢ ወይዘሮ ኪሚያ ጁንዲ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂክማ ከይረዲን፣ የልማት አጋር ድርጅት ተወካዮች፣ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።

በዚህ ወቅት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች ኮከስ ሰብሳቢ ወይዘሮ ኪሚያ ጁንዲ እንዳሉት ሴቶች ለልማትና እድገት ትልቅ ሚና አላቸው።

ያለእድሜ ጋብቻ፣የሴት ልጅ ግርዛትና ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከል የተሰሩ ስራዎች ለውጥ እያስመዘገቡ ቢሆንም አሁንም ትኩረትን የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የሴቶችን ጥቃትና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል የሚሰሩ ስራዎችን ማጠናከርና ኃላፊነትን መወጣት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

ከዚህ አንጻር ምክር ቤቱ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያጠናክር አስታውቀዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂክማ ከይረዲን በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ከሴቶችና ህፃናት ጋር በተያያዘ በርካታ ህጎችን በማውጣትና ዓለም አቀፍ ህጎችን በመተግበር ላይ ትገኛለች ብለዋል።

አገራዊ ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ያለእድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛት ላይ በተሰራው የግንዛቤ ስራ ለውጥ መምጣቱንም ገልፀዋል።

ሚኒስቴሩ ተቋማት የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያከናውኑት ስራ ላይ ድጋፍና ክትትል እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ሪታ ቢሶናውት በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመካለከል እንዲሁም የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እያከናወነች ያለው ተግባር የሚበረታታ ነው ብለዋል።

የሴቶችን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን እንዲሁም ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ ለማረጋገጥ ለሚሰሩ ስራዎች የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚያጠናክርም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም