ቀጥታ፡

በድሬደዋ አስተዳደር በመጠናቀቅ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች የብልጽግና ጉዞ ስኬታማነት ማሳያ ናቸው

ድሬዳዋ፤መጋቢት 16/2017(ኢዜአ)፡-በድሬዳዋ ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች የብልጽግና ጉዞ ስኬታማነት ማሳያ መሆናቸው ተገለጸ።

የብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ ዋና ጽህፈት ቤት አመራር አባላት በድሬደዋ እየተጠናቀቁ ያሉ የልማት ስራዎችን ዛሬ ተመልክተዋል።

ወጣቶች ከተመለከቷቸው የልማት ፕሮጀክቶች መካከል የተለያዩ መሠረተ ልማቶች፣የሌማት ትሩፋት፣የከተማ ግብርና እና የኮሪደር ልማት እና የኢትዮጵያ አየር ኃይል ድሬዳዋ የስራ እንቅስቃሴዎች ተጠቃሾቹ ናቸው።

በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉት የብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ ዋና ጽህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ገዛኽኝ አንዳርጌ እንደተናገረው፥አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በወጣቶች ተሳትፎ የተከናወኑ የልማት ስራዎች አበረታች ናቸው።

እነዚህ የልማት ስራዎችም አገራዊ ለውጡ የብልፅግና ጉዞው እውን መሆናቸውን ማሳያ እንደሆኑ ገልጿል።

ወጣቶቹ ለድሬዳዋ ኮሪደር ልማት ያላቸውን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉም አመልክቷል።

የብልጽግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ የወጣቶች ክንፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙህዲን አብዱራህማን በበኩላቸው፥ወጣቶች አገር አቀፍ የልማት ኢኒሼቲቮችን ከዳር ለማድረስ የተቀናጀ ርብርብ እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል።

ወጣቶቹ ያደረጉት ጉብኝትም ሀገራዊ ለውጡ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጣቸውን ይበልጥ እንዲረዱ ማገዙን ተናግረዋል።

ለአብነትም በአየር ኃይል ድሬዳዋ ምድብ ተገኝተው የተመለከቱት የአደረጃጀትና የቴክኖሎጂ ለውጥ የአገርን ሉአላዊነት ለማፅናት ያለን ሀገራዊ አቅም ያመላከተ እንደሆነም አንስተዋል።

በጉብኝቱ ከተሳተፉት ወጣቶች መካከል ፈልመታ መሐመድ እና ገላኒ አብዱልአዚዝ በሰጡት አስተያየት፤አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በድሬደዋ እየተከናወኑ የሚገኙ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች ህብረተሰብ ተጠቃሚ እያደረጉ መሆናቸውን እንደተረዱ ገልጸዋል።

በወጣቶች ተሳትፎ እየተከናወኑ የሚገኙትን ልማቶች በተቀናጀ መንገድ ለማሳካት ድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም