የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ከአሜሪካ የድንበር ቁጥጥር ፕሮግራም ኃላፊ ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ከአሜሪካ የድንበር ቁጥጥር ፕሮግራም ኃላፊ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 16/2017(ኢዜአ)፦ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የድንበር ቁጥጥር የመረጃ ስርዓት ፕሮግራም (PISCES) ኃላፊ ናታሊ ሲምፕሰን ከተመራ ልዑካን ቡድን ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
ውይይቱ ኢትዮጵያና አሜሪካ በአየር እና የብስ የድንበር ቁጥጥር ያላቸውን ትብብር ማጠናከር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።
የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት አሜሪካ ለኢትዮጵያ በአየር እና የብስ የድንበር ቁጥጥር ላደረገችው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው ትብብሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የድንበር ቁጥጥር የመረጃ ስርዓት ፕሮግራም (PISCES) ኃላፊ ናታሊ ሲምፕሰን ኢትዮጵያ በድንበር ቁጥጥር ላይ እያከናወነች ያለው ስራ አበረታች መሆኑን ገልጸዋል።
በፕሮግራሙ አማካኝነት በቀጣይ ለኢትዮጵያ ድጋፍ የማድረግ ፍላጎት እንዳለ መናገራቸውን ከኢሜግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።