ቀጥታ፡

ፈረንሳይ እና ኢትዮጵያ እየተተገበረ ላለው የሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳ የ28 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 16/2017 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ እና የፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ የሀገር በቀል የማክሮ ሪፎርም አጀንዳ ምዕራፍ ሁለት ትግበራን የመደገፍ አላማ ያለው የ28 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ የፋይናንስ ስምምነት ተፈራርመዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እና የልማት ኤጀንሲው የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሉዊስ-አንቶዋን ሱቼት ስምምነቱን ዛሬ ይፋ አድርገዋል።

የ25 ሚሊዮን ዩሮው ስምምነት እ.አ.አ ዲሴምበር ወር 2024 የተፈረመ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 10 ሚሊዮን ዩሮው አስቀድሞ ተለቋል።

ከ2024ቱ የፋይናንስ ስምምነት ውጪ ያለው የ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ የቴክኒክ ድጋፍ የስምምነት ፊርማ ዛሬ ተከናውኗል።

የገንዘብ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በጋራ የሚያስተባብሩት የቴክኒክ ድጋፍ ለሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳሁለተኛ ምዕራፍ ትግበራ የሚውል መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የፋይናንስ ዘርፉን ማሻሻል፣የመንግስት ልማት ድርጅቶች ሪፎርም፣ የአቅም ግንባታ፣የመንግስት እና የግል አጋርነት ማዕቀፎች እና የተለያዩ ተቋማት የጋራ ኢኒሼቲቮችን መደገፍ የሪፎርሙ አንኳር ትኩረቶች ናቸው።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ስምምነቱ ለኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ ትብብር አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የበጀት ድጋፉ የፊስካል ጫናውን እንደሚያረግብ ጠቅሰው የፋይናንስ ተወዳዳሪነት እና ተቋማዊ አቅም ግንባታን በማሳደግ ለዘላቂ እድገት የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣም አመልክተዋል።

የልማት ኤጀንሲው ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ያቀረቡት ሚኒስትር ዴኤታው የልማት አጋሮች ድጋፋቸውን ውጤታማ ለማድረግ ፕሮግራማቸውን ከሀገራዊ ቅድሚያ ፍላጎቶች ጋር እንዲያጣጥሙ ጠይቀዋል።

የፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሉዊስ-አንቶዋን ሱቼት የኢትዮጵያን ትራንፎርሜሽን እንዲሁም የአስተዳደር እና የውጤታማነት አቅምን የማሳደግ ድጋፍ ተገቢነት አንስተዋል።

ኤጀንሲው በቀጣይ በታክስ ዘርፍ፣ በሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም፣ ሎስስቲክስ እና ኢነርጂን ጨምሮ በቁልፍ ዘርፎች ድጋፍ የማድረግ ፍላጎት እንዳለው መግለጻቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም