ቀጥታ፡

ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀልን ለመከላከል የተደራጀ የመረጃና ነፃ የስልክ ጥሪ ማዕከል ተከፈተ

አዲስ አበባ፤መጋቢት 16/2017(ኢዜአ)፦የፍትህ ሚኒስቴር በሰው የመነገድና በህገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከል ያደራጀውን የመረጃና ነፃ የስልክ ጥሪ ማዕከል በይፋ ስራ አስጀምሯል።

8797 የመረጃና ነጻ የጥሪ ማዕከሉ ኢ- መደበኛ የሆነ ፍልሰትን ለመከላከል አቅም የሚፈጥር መሆኑ ተገልጿል፡፡

የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ ሰዎች ህጋዊ መንገድን ሳይከተሉ ከሀገር ለመውጣት የሚሞክሩባቸው ሁኔታዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በዚህም ሳቢያ ሰዎች ለማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ እና ለስነ ልቦናዊ ጉዳቶች ተጋላጭ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ችግሩ በዜጎችና በሀገር ላይ አሉታዊ ተጽእኖ የሚያሳድር በመሆኑ መንግስት ህገ ወጥ ፍልሰትን በመከላከል ህጋዊ አካሄድን ለማስፈን ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ማዕከሉ ዜጎች ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ መረጃ ሲኖራቸው በቀላሉ ለሚመለከተው አካል ጥቆማ የሚያደርጉበትን አቅም ከመፍጠሩ ባለፈ መንግስት ወንጀለኞቹን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ የሚከተለው ሂደት የሚያቀላጥፍ መሆኑን አክለዋል።

ነጻ የስልክ ጥሪ ማዕከሉ ከህገ ወጥ ፍልሰት ጋር ተያይዞ ተጎጂ የሆነ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚደርስባቸውን የጤና፣የማህበራዊና የስነ-ልቦና ጉዳት ለመፍታት የሚረዱ መረጃዎች ይሰጡበታል፡፡

በዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት የኢትዮጵያ ተልዕኮ ኀላፊ አቢባቶው ዋኔ በበኩላቸው፥ ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ኢ-መደበኛ ለሆነ ፍልሰት እንደሚዳረጉ ጠቅሰው፥ ችግሩ በርካቶችን ለሰብአዊ መብት ጥሰት እየዳረገ ያለ አሳሳቢ ጉዳይ ነው ብለዋል።

ችግሩን ለመቅረፍ የተደራጀው የመረጃና ነፃ የስልክ ጥሪ ማዕከል በይፋ ስራ መጀመር የሚበረታታ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

ተቋማቸው ህገ ወጥ ፍልሰትን ለመከላከል የሚሰሩ ተግባራት ፍሬያማ እንዲሆኑ ከኢትዮጵያ ጋር የሚሰራቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል እና ልየ ልዩ እገዛዎችን ለማድረግም ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቀዋል።

ህብረተሰቡ ማንኛውንም መረጃ በአማርኛ ፣በኦሮሚኛ ፣በትግርኛ እና በእንግሊዘኛ ማቅረብ እንደሚችል በመርሀ ግብሩ ላይ ተገልጿል።

በመድረኩ 8797 ነፃ የስልክ ጥሪ ማዕከልን በይፋ ለመጀመር ትልቅ ሚና ለተጫወቱት ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት እና ኢትዮ ቴሌኮም ምስጋና ቀርቦላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም