ለዜጎች ሥራ ዕድል ፈጠራ ከግሉ ዘርፍ ጋር የሚከናወኑ የትብብር ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ- ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 16/2017(ኢዜአ)፦ ለዜጎች ሥራ ዕድል ፈጠራ ከግሉ ዘርፍ ጋር የሚከናወኑ የትብብር ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና ሀይብሪድ ዲዛይን (ራይድ) በፈጠራ፣ በሥራ ዕድል እና በክህሎት ልማት ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል እና ለአምስት ዓመታት የሚቆይ መሆኑ ተገልጿል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ መንግስት ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ ነው።


 

በዚህ ሂደት የግሉ ዘርፍ ያለው ሚና አይተኬ በመሆኑ ሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ በትብብር የሚከናወኑ ተግባራት መኖራቸውን ነው ያብራሩት።

ከሀይብሪድ ዲዛይን ጋር የተደረሰው የመግባቢያ ስምምነት በቴክኖሎጂ ዘርፍ ለበርካታ ወጣቶች፣ ሴቶችና አካል ጉዳተኞች የስራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል እንደሆነም ጠቁመዋል።

የሀይብሪድ ዲዛይን (ራይድ) መስራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሳምራዊት ፍቅሩ በበኩላቸው፥ ድርጅታቸው በትራንስፖርት ቴክኖሎጂ ዘርፍ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል እየፈጠረ መሆኑን ገልፀዋል።


 

ስምምነቱ የቴክኖሎጂ ትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ያለውን አስተዋፅዖ ለማሳደግ ያለመ ነው ብለዋል።

በዚህም መሰረት ሀይብሪድ ዲዛይን ከራይድ ውጭ ሌሎች ፕሮጀክቶችን በመንደፍ ለበርካታ ለዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም