ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረትን የቁጥጥር ደንብን የተከተለ ምርት ማቅረብ የሚያስችል አረንጓዴ ኢኮኖሚ እየገነባች ነው

አዲስ አበባ፤መጋቢት 16/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረትን የደን ጭፍጨፋ ቁጥጥር ደንብ የተከተለ ምርትን ለገበያ ማቅረብ የሚያስችል አረንጓዴ ኢኮኖሚ እየገነባች መሆኗን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ እንዳለው መኮንን ገለጹ፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የመንግስትና የግሉ ዘርፍ ተዋንያን የአውሮፓ ህብረት የደን ጭፍጨፋ ቁጥጥር ደንብ ገቢራዊ ለማድረግ ሊወሰዱ በሚባቸው እርምጃዎች ዙሪያ የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡

የአውሮፓ ህብረት በ2050 በአውሮፓ ሀገራት የአረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት የአውሮፓ ህብረት የደን ጭፍጨፋ ቁጥጥር ደንብ አውጥቷል፡፡

የአውሮፓ ህብረት የደን ጭፍጨፋ ቁጥጥር ደንብ /EUDR/ ከተለያዩ ዓለማት ወደ አውሮፓ ሀገራት የሚገቡ ምርቶች ከደን ጭፍጨፋ ነጻ በሆነ መንገድ የተገኙ መሆን አለመሆናቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው።

ደንቡ በደን ምንጠራ የተገኙ ምርቶች ወደ አውሮፓ እንዳይገቡ ክልክላ ይደረጋል።

በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ አሉታዊ አስተዋጽኦ ያላቸው የካካዋ፣ ቡና፣ የቀንድ ከብት፣ የፕላስቲክ፣ እንጨት እና የምግብ ዘይት ምርቶች ወደ አውሮፓ ገበያ ሲገቡ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ እንዳለው መኮንን እንደገለጹት፤ የአውሮፓ ህብረት ወደ አባል ሀገራት የሚገቡ ምርቶች የህብረቱን ህግጋት ያከበሩ እንዲሆኑ አሰራር ዘርግቷል፡፡

በኢትዮጵያ ቡና፣የጥራጥሬና የቅባት እህሎች እንዲሁም ሌሎች ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ለማምረት የጋራ መግባባት መፍጠር ይገባል ብለዋል፡፡

የአውሮፓ ህብረት የደን ጭፍጨፋ ቁጥጥር ደንብን ተግባራዊ ለማድረግ መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸው፤ የኢትዮጵያ ብዝኃ የአየር ሁኔታ ምቹ እድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይልን በመጠቀም፣የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በአንድ አካባቢ በመገንባት ዘመናዊ የፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓት እንዲኖራቸው በማድረግ በቂ ዝግጅት ማድረጓን ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ ነጋዴዎች፣ አምራቾች፣ የተለያዩ አንቀሳቃሾች እና በዘርፉ የእሴት ሰንሰለት የሚሳተፉ ተዋንያን ግንባዜ መያዝና በትብብር መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የጥራት መሰረተ ልማት ፕሮጀክት አስተባባሪ ግርማ ማሞ፤ የኢትዮጵያ የቡና ምርት በአውሮፓ ህብረት የደን ጭፍጨፋ ቁጥጥር ደንብ ከተካተቱት ምርቶች መካከል መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ ከምታቀርባቸው ምርቶች እስከ 35 በመቶ ድርሻ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡

የቁጥጥር ደንቡ የመሬት አጠቃቀም ስርዓትን ለማጎልበት እና የኢትዮጵያን ምርት ለዓለም ገበያ ለማስተዋወቅ ያግዛል ብለዋል፡፡

በአውሮፓ ገበያ እንደ ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ፣ ፍትሐዊ ንግድ እና መሰል ቢሮክራሲ ያለባቸውን መስፈርቶች ሰብሮ ለመግባት ዕድል የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም