ኢትዮጵያና ፓኪስታን በፓርላሜንታዊ ዲፕሎማሲ የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ፓኪስታን በፓርላሜንታዊ ዲፕሎማሲ የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 16/2017 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን ፓርላሜንታዊ ዲፕሎማሲን በመጠቀም የሁለትዮሽ ትብብራቸውን የበለጠ ለማጎልበት እንደሚሹ አስታወቁ።
በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር ከፓኪስታን ሴኔት ሊቀመንበር ሰይድ ዩሱፍ ራዛ ጊላኒ ጋር ዛሬ በኢስላማባድ ተወያይተዋል።
ውይይቱ ኢትዮጵያና ፓኪስታን በሁለትዮሽ እና በባለብዝሃ ወገን የትብብር አማራጮች ያላቸውን ትብብር ማጠናከር በሚችሊበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው።
አምባሳደር ጀማል ለሴኔት ሊቀመንበሩ ኢትዮጵያ በቀጣናዊ ትስስር፣ ሰላምና መረጋጋት እና ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ከጎረቤት ሀገራት ጋር እያደረገች ያለውን ጥረት አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።
ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ምርታማነትን እየጨመረ እና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን እያሳደገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
በኢንቨስትመንት፣ ንግድ፣ ባህል፣ አቪዬሽን፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ያላቸው የሁለትዮሽ ትብብር እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
የሴኔት ሊቀመንበሩ እ.አ.አ በሜይ ወር 2025 በአዲስ አበባ በሚካሄደው የኢትዮጵያን ምርቶችና አገልግሎት የሚያስተዋውቅ ኤግዚቢሽን እንዲሳተፉ ጋብዘዋል።
የፓኪስታን ሴኔት ሊቀመንበር ሰይድ ዩሱፍ ራዛ ጊላኒ ፓኪስታን ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ግንኙነት ትልቅ ዋጋ እንደምትሰጥ ገልጸው የሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ እና የባለብዝሃ ወገን ትብብርን ለማጠናከር እንደምትሻ ተናግረዋል።
ጊላኒ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአመራር ሰጪነታቸው ኢትዮጵያ በቀጣናዊና ዓለም አቀፍ መድረኮች ያላት ሚና እንዲለወጥ እና የማህበረ-ኢኮኖሚ ለውጥ እንድታመጣ ያደረጉትን አስተዋጽኦ አድንቀዋል።
በውይይቱ ሀገራቱ በፓኪስታን ሴኔት የወዳጅነት ቡድን ማቋቋምን ጨምሮ በፓርላሜንታዊ ዲፕሎማሲያዊ ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ከስምምነት ላይ መደረሱን በኢስላማባድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እ.አ.አ በ1973 እንደጀመሩ መረጃዎች ያመለክታሉ።