የህዝብን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች እንዲጠናከሩ የበኩላችንን እንወጣለን--የሚዛን አማንና የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የህዝብን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች እንዲጠናከሩ የበኩላችንን እንወጣለን--የሚዛን አማንና የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎች
ሚዛን አማን/ወልቂጤ፤ መጋቢት 16/2017(ኢዜአ)፡-የህዝብን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች እንዲጠናከሩ የበኩላቸውን እገዛ እንደሚያደርጉ የሚዛን አማንና የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ነዋሪዎቹ ባለፉት ዓመታት ለመሰረተ ልማት ግንባታ የተሰጠው ትኩረትና እየታየ ያለው ለውጥም የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስትን ግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ከምክር ቤቱ አበላት ለቀረቡላቸው የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ መስጠታቸው የሚታወስ ነው።
በዚህ ወቅትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት የህዝብን ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት ለሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።
በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሚዛን አማን እና የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎች የህዝብን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ የልማት ሥራዎች ተጠቃሚ በመሆናቸው ልማቱ እንዲጠናከር የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
ከሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ከፍያለው ምትኩ እንደገለጹት፣ በየአካባቢው የህዝብን የልማት ጥያቄ በመመለስ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ሁለንተናዊ ልማትን ለማፋጠን የተጀመሩ ሥራዎች ህዝብን ተጠቃሚ እያደረጉ በመሆኑ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
የልማት ሥራው ለሚዛን አማን ከተማ መነቃቃትን ፈጥሯል ያሉት ነዋሪው፣ "በአሁኑ ወቅትም በመንግስትና በግሉ ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ከተማዋን አንድ እርምጃ ያሻግራሉ" ብለዋል።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የታየው ፍትሃዊ የልማት ተደራሽነት በአካባቢያቸውም ልማት እንዲጠናከር ማድረግን የገለጹት ደግሞ አቶ ኃይሉ ኑርልኝ የተባሉ ነዋሪ ናቸው።
በሚዛን አማን ከተማ እየተከናወኑ ካሉ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች መካከል የሚዛን አማን አየር ማረፊያና የገበታ ለትውልድ አካል የሆነው የደንቢ ሎጅን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
"በአሁኑ ወቅትም የከተማዋን ገጽታ እየቀየረ ላለው የኮሪደር ልማት የገንዘብና የሀሳብ ድጋፍ በማድረግ የበኩላችንን እየተወጣን ነው" ብለዋል።
ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ብርሃኑ ጋወራሻ በበኩላቸው፣ "ከዚህ ቀደም አይተን የማናውቀው ልማት ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ እያየን ነው" ብለዋል።
ኢትዮጵያን ከፍ የሚያደርጉ ጉልህ የልማት ሥራዎች በአዲስ አበባና በክልል ከተሞችም ጎልተው እየታዩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የተመዘገቡ የልማት ውጤቶች ህዝብን ተጠቃሚ እያደረጉ በመሆናቸው ልማቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከመንግስት ጎን ሆነው የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
በተመሳሳይ ዜና የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎችም በመንግስት እየተከናወኑ ባሉ የልማት ሥራዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ሀዲሞ ሀሰን እንዳሉት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ለመሰረተ ልማት በተሰጠው ትኩረት የልማት ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
ለእዚህም በክልሉ ከአጣጥ - ሌራ ያለው የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክት የህብረተሰቡን የረዥም ጊዜ ጥያቄ የመለሰና የተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች ያስተሳሳረ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
የልማት ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰርቶ ማጠናቀቅ ልምድ እየሆነ መምጣቱም ይበልጥ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸውም ነው የገለጹት።
ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ሳምሶን ለገሰ በፌደራል መንግስት የተከናወኑ የመንገድ ፕሮጀክቶች ለክልሉ የኢንቨስትመንት እድገት እንዲሁም ለህብረተሰቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል።
የፍጥነት መንገድን ተደራሽ ለማድረግ የተጀመረውን ሥራ አድንቀው፣ በክክልና በዞን ጭምር የተገነቡ ሆስፒታሎች አርሶ አደሩ አገልግሎት ፍለጋ ርቆ ሲሂድ ይደርስበት የነበረውን እንግልት ማስቀረታቸውን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክር ቤት የዜጎችን ፍትሀዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማስፈን መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የገለጹበት መንገድ ተገቢ እንደሆነና የአካባቢያቸው ልማት ለእዚህ አንድ ማሳያ መሆኑንም ተናግረዋል።
ሌላው የወልቂጤ ከተማ ነዋሪ አቶ አብድልበር ናስር “የኮሪደር ልማት ሥራ የአካባቢውን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት ያስገባ ሆኖ የተቀናጀ መሰረተ ልማት ግንባታ የታየበት ነው” ብለዋል።
በተለይ በክልሉ ቡታጀራ፣ ሆሳዕናና ወልቂጤ ከተሞች የተከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎች የአመራር፣ የባለሙያውና እና የህብረተሰቡ ትብብርና ቅንጅት የታየበት መሆኑን ነው የገለጹት።
የኮሪደር ልማት ከዚህ ቀደም በልማት ሥራ ላይ ይስተዋል የነበረን መጓተት ያስቀረና ህብረተሰብ ተኮር ሥራዎች ጎልተው እንዲታዩ ማድረጉን ጠቁመዋል።