ቀጥታ፡

በአማራ ክልል በኢንቨስትመንት የሚሰማሩ ባለሃብቶች ቁጥር እያደገ መጥቷል - የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ

ባህር ዳር፤ መጋቢት 16/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ያሉትን የኢንቨስትመንት አማራጮች በመጠቀም የሚያለሙ ባለሃብቶች ቁጥር እያደገ መምጣቱን የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ገለጸ።

ቢሮው በክልሉ በበጀት ዓመቱ ያለፉት ወራት ከ251 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን ገልጿል።

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ዮሐንስ አማረ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ክልሉን የኢንቨስትመንት መዳረሻ ማድረግ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

ለዚህም የክልሉን የኢንቨስትመንት አማራጮች የመለየት፣ የማደራጀትና በተለያየ መንገድ ለባለሃብቱ የማስተዋወቅ እንዲሁም አሰራሮችን የማሻሻል ስራ ተሰርቷል ብለዋል።

በተከናወነው ጠንካራ ስራም ባለፉት ስምንት ወራት ከ294ሺህ 690 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችሉ ለ1ሺህ 547 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን ገልፀዋል።

የኢንቨስትመንት ፍቃዱም ከ251 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች መሰጠቱን ገልጸው ይህም የክልሉ ሰላም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱ የኢንቨስትመንት ዘርፉ እንዲያድግ እድል መፍጠር ማስቻሉንም ተናግረዋል።

ለባለሃብቶች እየተሰጠ ያለው የቅርብ እገዛ መሻሻሉን አመልክተው፤ ባለፉት ወራት 286 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የነበረባቸውን ችግሮች በመፍታት ወደ ማምረትና አገልግሎት እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል።

የመሬት አቅርቦት እጥረት ለነበረባቸው ፕሮጀክቶች 429 ሄክታር መሬት ማስተላለፍ እንደተቻለ ጠቅሰው፤ በተለይም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተሻለ አቅምና ልምድ ያላቸው ባለሃብቶች ወደ ክልሉ መጥተው በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ ማድረጉን አብራርተዋል።

እንዲሁም ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር የባለሃብቶችን የመንገድ፣ የውሃ፣ የሃይል አቅርቦት፣ የብድርና መሰል ችግሮችን መፍታት መቻሉን ጠቅሰዋል።

በክልሉ ያለውን የተሻለ ሰላም በመጠቀምም 509 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችም ወደ ግንባታና በቅድመ ግንባታ ሂደት ላይ እንደሚገኙ አቶ ዮሐንስ አስታውቀዋል።

በቀጣይም ባለሃብቶችን በቅርበት በማገዝ በግብርና፣ ሆርቲካልቸርና መሰል ዘርፎች በስፋት እንዲሰማሩ ተገቢው እገዛና ድጋፍ እንደሚደረግ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም