የኪነ-ጥበብ ስራዎች ሀገር በቀል የሆኑ እሴቶች ማስተዋወቅና ማሳደግ ላይ ሊያተኩሩ ይገባል - የኪነጥበብ ባለሙያዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኪነ-ጥበብ ስራዎች ሀገር በቀል የሆኑ እሴቶች ማስተዋወቅና ማሳደግ ላይ ሊያተኩሩ ይገባል - የኪነጥበብ ባለሙያዎች

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 16/2017(ኢዜአ)፡- ኪነ-ጥበብ ስራዎች ሀገር በቀል ባህላዊ እሴቶችን በማስተዋወቅ በኩል ይበልጥ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ተናገሩ።
ኪነ-ጥበብ የሰውን ልጅ የሕይወት ተሞክሮ በማጉላትና ሙያዊ በሆነ መንገድ እውነትንና ውበትን መሠረት በማድረግ የሚቀርብ የፈጠራ ውጤት ነው።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ኪነ-ጥበብ የሀገር ባህልና እሴት የሚገልጽ የጥበብ ውጤት መሆኑን ይገልጻሉ።
የህዝብ ለህዝብ ትስስርን በማጠናከርና፣ ሰላምና አንድነትም በመፍጠር ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወትም እንዲሁ።
ባህላዊ እሴቶችን ከማስተዋወቅና ከማሳደግ አንጻር ኪነ-ጥበብ ትልቅ ድርሻ እንደሚያበረክት የኪነጥበብ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ተዋናይ ሰለሞን ሀጎስ ለኢዜአ እንደገለጸው የኪነ-ጥበብ ውጤቶች ትኩረት የሚያደርጉት የማህበረሰቡ ባህላዊ እሴቶች ላይ ነው።
በኢትዮጵያ የተለያዩ እምቅ ባህላዊ እሴቶች መኖራቸው ለኪነ-ጥበቡ ዘርፉ ምቹ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ሌላኛው አርቲስት ማህተመ ኃይሌ በበኩሉ፤ የሰለጠኑ ሀገራት ስልጣኔያቸውና ባህላቸውን ለዓለም የሚያስተዋወቁበት መሳሪያዎች መካከል አንዱ ኪነ-ጥበብ መሆኑን ገልጿል።
ኪነ-ጥበብ የኢትየጵያን ባህልና እሴት ለአለም በማስተዋወቅ በኩል ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ተናግሯል።
ተዋንያኖቹ ይህ እምቅ ባህላዊ እሴትና ታሪክ በኪነ-ጥበቡ ዘርፍ መሰራትና መተዋወቅ የሚገባቸውን ያህል እንዳልተሰራባቸው ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም በቀጣይ የዘርፉ ባለሙያዎች ሀገር በቀል የሆኑ እሴቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ማስተዋወቅና ማሳደግ በሚገባው ልክ እንዲሰሩ ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱርዝም ቢሮ የኪነ-ጥበብ ሃብቶች ልማት፤ የመድረኮችና ኩነቶች ዝግጅት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ደኑ በበኩላቸው፤ ቢሮው የኪነ-ጥበብ ሃብቶችን የማልማት እና ኢንዱስትሪውን የማበልጸግ ተግባር እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ህብረተሰቡ የኪነ-ጥበብ ውጤቶችን እንዲያገኝና የዘርፉ ባለሙያዎችም ክህሎታቸውና ልምዳቸውን እንዲያጎለብቱ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በሀገራችን የሚገኙ ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶች በሚገባቸው ልክ ማልማትና ማስተዋወቅ የሚያስችሉ ስራዎችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
በከተማው በተለያዩ መድረኮች የሚቀርቡ የኪነ-ጥበብ ውጤቶች ሰላምን፣ ገዥ ትርክትንና አንድነትን በሚያጎልብቱ መልኩ እንዲቀርቡ የማድረግ ስራም በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን አመላክተዋል።