አሰባሳቢ ትርክት የሰዎች አብሮነትና የማንነት እሴት እንዲጎለብት ያግዛል - ዲያቆን ዳንኤል ክብረት - ኢዜአ አማርኛ
አሰባሳቢ ትርክት የሰዎች አብሮነትና የማንነት እሴት እንዲጎለብት ያግዛል - ዲያቆን ዳንኤል ክብረት
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 16/2017(ኢዜአ)፦አሰባሳቢ ትርክት የሰዎች አብሮነትና የማንነት እሴት እንዲጎለብት ያግዛል ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሚኒስትር ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ገለጹ።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወልቂጤ ከተማ ውጤታማ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ለገዢ ትርክት በሚል መሪ ሃሳብ ለሚዲያና ኮሙኒኬሽን አመራሮች ስልጠና እየተሰጠ ነው።
በስልጠናው ላይ ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እንደገለጹት ገዢ ትርክት የሀገርን ታሪክ የወደፊት ተስፋ እና ዛሬ ላይ የሚኖረውን ሚና የሚከሰቱ ክስተቶችን የምንመለከትበት ነው።
አሰባሳቢ ትርክት የሰዎችን አብሮነት፣ የማንነት እሴት እንደሚያጎለብትም ገልጸዋል።
ገዢ ትርክት በህዝብ ውስጥ የላቀ የልማት ተነሳሽነት፣ የአብሮነት እና የወንድማማችነት መልካም ትስስር እንደሚፈጥርም አመላክተዋል።
የሀገሪቱን የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወሰነው በትርክት ስለመሆኑ እና የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ይህን በማጉላት የህዝቡ አብሮነት እና መልካም እሴቶች እንዲጎለብቱ ማገዝ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
በስልጠናው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሃላፊና የክልሉ መንግሥት ዋና ተጠሪ ዲላሞ ኦቶሬ(ዶ/ር)፣ የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ ዘሪሁን እሸቱ እና ሌሎች አመራሮች ተገኝተዋል።