ቀጥታ፡

የሶማሌና የአፋር ክልሎች ህዝቦችን የወንድማማችነት ግንኙነት ማጠናከሪያ መድረክ መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 16/2017(ኢዜአ)፡- የሶማሌና የአፋር ክልሎች ህዝቦችን የወንድማማችነት ግንኙነት ማጠናከሪያ መድረክ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

በመድረኩ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ(ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ኀላፊ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ፣ ከሁለቱ ክልሎች የተውጣጡ ምሁራን፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ታድመዋል።

ትናንት በተካሄደው የቅድመ ምክክር መድረክ የሰላም ሚኒስትር አቶ መሀመድ እድሪስ ተገኝተው እንደተናገሩት፤ የሶማሌና የአፋር ክልሎች ህዝቦች የጋራ ታሪክ ያላቸው ለብዙ ዘመናትም በፍቅርና በአብሮነት የተሻገሩ ናቸው።


 

አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመፍታት ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና የጋራ ልማትን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን በወቅቱ ገልጸዋል።

የወንድማማችነት መድረኩ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ መፍትሔ በመስጠት መግባባትንና የጋራ ልማትን ለማጠናከር ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረውም ነው የጠቀሱት።

የክልሎቹ ህዝቦች በጋራ የመልማት፣ የማደግና የመበልጸግ አቅም ያላቸው መሆናቸውን የሰላም ሚኒሰትሩ መግለጻቸውም እንዲሁ።

ዛሬን ጨምሮ ለሚቀጥሉት ሁለት ቀናት በሚካሄደው መድረክ ላይ የሁለቱን ክልሎች ህዝቦች የወንድማማችነት ግንኙነት የሚያጠናክሩ የውይይት መነሻ ሃሳቦች ቀርበው ምክክር የሚደረግባቸው ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም