ኢትዮጵያ በጉባዔው በሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ላይ ያስመዘገበቻቸውን ስኬቶች የተመለከተ ተሞክሮ አቅርባለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በጉባዔው በሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ላይ ያስመዘገበቻቸውን ስኬቶች የተመለከተ ተሞክሮ አቅርባለች
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 16/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና መቀመጫ ኒውዮርክ ሲካሄድ በቆየው 69ኛው ዓለም አቀፍ የሴቶች ጉባኤ በሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ላይ ያስመዘገበቻቸውን ስኬቶች የተመለከተ ተሞክሮ አቅርባለች።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና መቀመጫ ኒውዮርክ ሲካሄድ የቆየው 69ኛው ዓለም አቀፍ የሴቶች ጉባኤ(Commission on the Status of Women) የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቋል።
ጉባዔው በዋነኝነት የቤጂንግ መግለጫና የድርጊት መርሃ ግብር ፀድቆ በስራ ላይ የዋለበት 30ኛ ዓመትን በማስመልከት የድርጊት መርሃ ግብሩን አፈፃፀም መገምገም ላይ ያተኮረ ነው።
በዚህም ጉባዔው በስርዓተ ጾታ እኩልነት ትኩረቱን ባደረገው የቤጂንግ መግለጫ እና የድርጊት መርሃ ግብር ቀጣይ አምስት ዓመት የትግበራ ምዕራፍን አፅድቋል።
ኢትዮጵያም ከተለያዩ መንግስታትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት የጎንዮሽ መድረኮችን ማዘጋጀቷን ከሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ከተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት(ዩኒዶ) ጋር በመሆንም በሴቶችና አረንጓዴ ኢኮኖሚ ላይ የተካሄደው ለአብነት የሚጠቀስ ነው።
ከተባበሩት መንግስታት የስነ ህዝብ ፈንድ፣ ከተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት እና ግሎባል ኤቪደንስ ከተሰኘ የስርዓተ ጾታ ተቋም ጋር በመተባበር በሴቶችና ታዳጊ ሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን ማስቆም የሚያስችሉ ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች ውይይቶች ተደርገዋል።
ከሞሮኮ ጋር በመሆን የገጠር ሴቶችን በመደገፍ ዘላቂ የልማት ግቦችን ማሳካት ላይ ያተኮሩ መድረኮችም ተካሂደዋል።
የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ በስርዓተ ጾታ እኩልነት፣ ሴቶች ተሳትፎ እና ውሳኔ ሰጪነት ላይ ስኬታማ ስራዎችን ማከናወኗን በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት ገልጸዋል።
የቤጂንግ መግለጫና የድርጊት መርሃ ግብር እ.ኤ.አ በ1995 በ11 ጉዳዮች ላይ ያተኮረና በዋነኝነት የስርዓተ ፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ እና ሴቶችን ለማብቃት የወጣ ሰነድ ነው።
በጉባኤው ላይ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድንን ጨምሮ የመንግስት ተወካዮች፣ ከተለያዩ የሲቪክ ማህበራት፣ የሴቶችና ወጣቶች ድርጅቶች፣ የጥናትና ምርምር ተቋማት፣ አለም አቀፍና አህጉራዊ ድርጅቶች የተውጣጡ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።
ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2025 ለሚካሄደው 70ኛው ዓለም አቀፍ የሴቶች ጉባኤ አፍሪካን በመወከል የኮሚቴው አባል ሆና መመረጧን ሚኒስቴሩ በመረጃው አስታውሷል።