ከ 580 ሺህ በላይ ዜጎች የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ስልጠናን በመከታተል ላይ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
ከ 580 ሺህ በላይ ዜጎች የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ስልጠናን በመከታተል ላይ ናቸው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16/2017(ኢዜአ)፦በአገር አቀፍ ደረጃ ከ 580 ሺህ በላይ ዜጎች የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ስልጠናን በመከታተል ላይ መሆናቸውን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ስልጠናውን ያጠናቀቁ ከ180 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች የምስክር ወረቀት ማግኘታቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
መርኃ ግብሩ በኢትዮጵያ መንግስትና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እገዛ የሚተገበር የዲጂታል ሥራ ክህሎት ማሳደጊያ የትብብር ፕሮጀክት ነው።
ፕሮጀክቱ "ትውልድ ይማር፣ ትውልድ ይሰልጥን፣ ከዓለም ጋር ይፎካከር" በሚል እሳቤ ዜጎች የቴክኖሎጂ እውቀታቸውን በማዳበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ብቁ እንዲሆኑ እየተተገበረ ይገኛል፡፡
ፕሮጀክቱ በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት አምስት ሚሊየን ኢትዮጵያውያንን በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ በአንድሮይድ ማበልፀግ፣ ዳታ ሳይንስና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎት እንዲጨብጡ የሚያስችል ነው።
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የአይሲቲና ዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ይሹሩን አለማየሁ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤መርኃ ግብሩ የዲጂታል ክህሎትን ለመገንባት የሚያስችል ነው።
በመርኃ ግብሩ ከ 580 ሺህ በላይ ዜጎች ተመዝግበው ስልጠና እየተከታተሉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 180 ሺህ የሚሆኑት የምስክር ወረቀት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋና ሐረር የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ስልጠና አፈፃፀም የተሻለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
መርኃ ግብሩን የተሳካ ለማድረግ ሌሎች ክልሎች በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበው ሚኒስቴሩም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።
ስልጠናው የፈጠራ ስራን ለማበረታታት የሚያግዝ በመሆኑ በተለይ ወጣቶች ይህን እድል ተጠቅመው ራሳቸውን ማብቃት እንዳለባቸው አስረድተዋል።