ኮሚሽኑ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙን በቴክኖሎጂ የማዘመን ስራውን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙን በቴክኖሎጂ የማዘመን ስራውን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - ቋሚ ኮሚቴው
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15/2017(ኢዜአ)፦ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሀገራዊ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙን በቴክኖሎጂ ለማዘመን እያከናወነ ያለውን ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
ቋሚ ኮሚቴው የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የሪፎርም ስራዎችን ጎብኝቷል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ(ዶ/ር) ኮሚሽኑ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም በቴክኖሎጂ በማዘመን ለትውልድ የሚተላለፍና የተደራጀ መረጃ አያያዝን የተከተለ እንዲሆን የጀመራቸውን ተግባራት ማጠናከር እንደሚኖርበት ገልጸዋል።
ሪፎርሙ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቅሰው የህግ ማዕቀፎች በሚገባ መተግበር እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።
የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሸነር መኩሪያ ኃይሌ(ዶ/ር) በበኩላቸው ሲቪል ሰርቫንቱ ኢትዮጵያን የሚመጥን፣ ትውልድ ተሻጋሪ እና የተደራጀ መረጃ አያያዝን የተከተለ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ሀገራዊ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮዎች መወሰዱን ጠቁመዋል።
የሰው ኃይል መረጃና ስምሪቱን ማስተካከል የሚያስችል የዲጂታላይዜሽን እንዲሁም የግልጽነትና ተጠያቂነት አሰራር መዘርጋት እንደተቻለም አመልክተዋል።
በፌደራል ደረጃ የተጀመረው ሪፎርም በክልሎችም እንደሚቀጥል አክለዋል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት የኮሚሽኑን የተለያዩ የስራ ክፍሎች እና አገልግሎቶች መጎብኘታቸውን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።