ቀጥታ፡

በንብ ማነብ ዘርፍ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ላይ ያተኮረው መርሃ ግብር አበረታች ውጤት እየተመዘገበበት ነው - ግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 15/2017(ኢዜአ)፡- በንብ ማነብ ዘርፍ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ላይ ያተኮረው መርሃ ግብር አበረታች ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በንብ ማነብ ዘርፍ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ላይ ያተኮረው መርሃ ግብር የአምስት ዓመት ጉዞ እና በመርሃ ግብሩ የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች ልምዳቸውን ያካፈሉበት መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።


 

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ግርማ ሙሉጌታ በወቅቱ እንዳሉት፤ በርካታ ወጣቶች በንብ ማነብ ዘርፍ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ የታገዙ ወጣቶች በማር፣ ሐር እና ተያያዥ የእሴት ሰንሰለቶች ላይ መሰማራታቸውን ጠቁመው፤ በተለይም የማር ምርት ለሀገር እና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜያት በንብ ማነብ ባህል የበለፀገች ሀገር መሆኗን ጠቁመው፤ ተግባራዊ በተደረገው የሌማት ትሩፋት ያላትን እምቅ አቅም በማውጣት መጠቀም መጀመሯንም ገልጸዋል፡፡


 

ሚኒስቴሩ በመርሃ ግብሩ የተያዙ ግቦች እንዲሳኩ አስፈላጊ ድጋፍ እና ክትትል እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።


 

የዓለም አቀፍ የነፍሳት ፊዚዮሎጂ እና ሥነ-ምህዳር ማዕከል ዳይሬክተር ጀነራል አብዱ ቴነኩአኖ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ መርሃ ግብሩ ተሞክሮዎች ለመለዋወጥ ብሎም አዳዲስ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዘርፉ ዕድገት የፋይናንስ፣ የገበያ ትስስር፣ የድርጅት ድጋፍ እና የፖሊሲ ማዕቀፎች የበለጠ አቅም የሚፈጥሩ መሆናቸውን ጠቁመው፤ የኢትዮጵያ መንግስት በዘርፉ የወጣቶችን የስራ ዕድል በማሳደግ ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።


 

ከመርሀ ግብሩ ተጠቃሚዎች መካከል ወጣት አብርሀም ሀብቱ እንዳለው፤ በተሰጣቸው ስልጠና ማርን በዘመናዊ እና በባህላዊ መንገድ በማምረት ላይ እንደሚገኙ ገልጿል።

በተደረገለት ድጋፍ አሁን ላይ ከ30 በላይ በሆኑ የንብ ቀፎዎች ማር እያመረተ እንደሚገኝ ተናግሯል፡፡


 

ሌላኛው ተጠቃሚ ዳዊት ጌቻ ከንብ ማነብ አጠቃቀም አንስቶ ንግድን ማስተዳደር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ስልጠና ማግኘቱን ገልጿል።


 

በተፈጠረላቸው የገበያ ትስስር ተጠቃሚ መሆኑን የገለጸው ደግሞ ሌላኛው የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ አወል መስጠት ነው።

አምስት ዓመት ያስቆጠረው በንብ ማነብ ዘርፍ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር መርሃ ግብር በማስተር ካርድ ፋውንዴሽንና በዓለም አቀፍ የነፍሳት ፊዚዮሎጂ እና ሥነ-ምህዳር ማዕከል ትብብር የሚደገፍ ነው።

በኢትዮጵያ ከባህላዊ የንብ ቀፎ ከአምስት እስከ ስድስት ኪሎ ግራም የማር ምርት የሚገኝ ሲሆን፤ ከተሻሻሉ ዘመናዊ ቀፎዎች ደግሞ ከ15 እስከ 40 ኪሎ ግራም የማር ምርት እንደሚገኝ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም