የጉራጌ ባህላዊ መንደር መልካም ልምድ የሚወሰድበት ነው- ቢቂላ ሁሪሳ(ዶ/ር)

ወልቂጤ፤ መጋቢት 15/2017 (ኢዜአ):- የጉራጌ ባህላዊ መንደር "ጀፎረ" መልካም ልምድ የሚወሰድበት ነው ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ዓለም አቀፍና የሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ።

ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በዞኑ ቸሀ ወረዳ የገጠር ኮሪደር ልማት "ጀፎረ"ን በጎበኙበት ወቅት፤ የጉራጌ ማህበረሰብ ነባር ባህል እና የአኗኗር እሴት ውስጥ አካባቢን በእቅድ የመምራት ጥበብ ለሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች ተምሳሌት ነው ብለዋል።


 

አካባቢን ጽዱና ውብ አድርጎ የማልማት ጥበብ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት የጉራጌ ማህበረሰብ ሲተገብር መቆየቱን አውስተዋል።

አካባቢው ወጣቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ማህበራዊ መስተጋብራቸውን የሚከውኑበት ስለመሆኑም መረዳታቸውን ጠቅሰዋል።

የጉራጌ ማህበረሰብ "ጀፎረ" ብሎ የሰየመው የገጠር ኮሪደር ልማት የስልጣኔ መገለጫ መሆኑን ነው ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) የተናገሩት።

እንደሀገርም ለተጀመረው የኮሪደር ልማት አጋዥ መሆኑን አንስተዋል።

ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በጉራጌ ዞን ቸሀ ወረዳ አስተፖ ቀበሌ የሚገኘውን የጠናቃ "ጀፎረ"ን የተመለከቱ ሲሆን፤ በዚህም የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልና የጉራጌ ዞን የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም