የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓትን ለማጠናከር ወቅታዊ የአየር ትንበያ መረጃዎች እየቀረቡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓትን ለማጠናከር ወቅታዊ የአየር ትንበያ መረጃዎች እየቀረቡ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 15/2017(ኢዜአ)፦የተፈጥሮ አደጋን ለመቀነስና ቅድመ ጥንቃቄን ለማጠናከር ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ወቅታዊና አስተማማኝ የአየር ትንበያ መረጃዎችን ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ "የቅድመ ማስጠንቀቂያ ጉድለቶችን በጋራ እንሙላ" በሚል መሪ ሀሳብ በኢትዮጵያ ለ44ኛ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ64ኛ ጊዜ የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ቀንን አክብሯል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመጠቀም አገልግሎቱን እያሻሻለ ይገኛል፡፡
የአየር ሁኔታን በመተንበይና በመተንተን አስተማማኝ መረጃዎችን በፍጥነት በማድረስ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ልማት እንቅስቃሴ ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየሰራ ነውም ብለዋል።
ለግብርና፣ ለውሃ፣ ለአቪየሽን እና ለጤና ዘርፍ አጋዥ የአየር ጠባይ መረጃዎችን እያቀረበ እንደሚገኝ በአብነት ጠቁመዋል።
የአየር ጠባይና ሁኔታ ቅደመ ማስጠንቀቂያ ስርዓትን በቴክኖሎጂ በማዘመንና እንደ ድርቅና ጎርፍ ያሉ አደጋዎችን ለመቀነስ የሚያስችሉ መረጃዎች ተደራሽ እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ የአየር ጠባይና ሁኔታ ቅደመ ማስጠንቀቂያ ስርዓትን ለማዘመን የሚያግዙ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙም አንስተዋል።
የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶች ላይ የሚታዩ ጉድለቶችን ለመሙላት የባለድርሻ አካላት ትብብርና ቅንጅት መጠናከር ወሳኝ እንደሆነም አመላክተዋል።
የዓለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት በሀገሪቱ ዘላቂ ልማትን ለማሳካት የአየር ጠባይ ለውጥን ለመቋቋምና የአደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት እየደገፈ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በዓለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ አህጉር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ተወካይ አቡበከር ሳሊህ (ዶ/ር) የቴክኒክና የአቅም ግንባታ ድጋፎችን ለኢንስቲትዩቱ እና ለውሃና ኢነርጂ ባለሙያዎች እየሰጠ መሆኑን አንስተዋል።
በተለይ በኢትዮጵያ የአየር ሁኔታ ትንበያ እና የውሃ ሀብት አጠቃቀምን ለማሻሻል ድርጅቱ በአጋርነት እየሰራ ነው ብለዋል።