ቀጥታ፡

በፕሮግራሙ የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

አዳማ ፤  መጋቢት 15/2017(ኢዜአ)፡- የከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮግራም አካል ጉዳተኞችን በማካተት  ተጠቃሚነታቸውን የሚያጎለብቱ ተግባራት  ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተከናወነ መሆኑን  የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ገለጸ።

የፌዴራል፣ የክልሎች፣ የአዲስ አበባና ድሬደዋ ከተማ አስተዳደሮች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበትና በፕሮግራሙ  የአካል ጉዳተኞች  አካታችነት  ላይ ያተኮረ  መድረክ በአዳማ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።


 

በከተማና መሰረተ  ልማት ሚኒስቴር የከተሞች ምግብ ዋስትናና ሴፍቲኔት  ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ብርሃኑ ተሾመ ፤ በከተሞች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ፕሮግራሙ በአሁኑ ወቅት በ88 ከተሞች ተግባራዊ እየተደረገ ነው ያሉት ሃላፊው፤  በዚህም ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተጠቃሚ በመሆን ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ይህም በአካባቢ ልማት ስራ በተለይ በደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገድ፣በከተሞች ማስዋብና አረንጓዴ ልማት ፣በፅዳት፣በተፋሰስ ልማትና በአነስተኛ መሰረተ ልማት ላይ በመሳተፍ እንደሆነ ገልጸዋል።

በተከሞቹ የፕሮግራሙ ተግባራዊ መደረግ ፅዳት፣ውበትና አረንጓዴ ልማት፣ጎርፍና የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ በአከባቢ ጥበቃ ላይ ውጤት እያመጣ መሆኑን አስረድተዋል።

አካል ጉዳተኞችን  አካታች እንዲሆን አሰራር ተዘርግቶ ተግባራዊ መደረጉን ገልጸው፤ በዚህም በሺህዎች የሚቆጠሩ አካል ጉዳተኞች  ታቅፈው በከተሞች ተጠቃሚ መሆናቸውን  ተናግረዋል።

ተጠቃሚነታቸውን የሚያጎለብቱ ተግባራት  ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተከናወነ መሆኑን ተመላክቷል። 

በዚህም ከጠባቂነት ወደ ልማትና ምርታማነት መሻገር እንዲችሉ ፕሮግራሙ  ቁልፍ አጋዥ መሆኑን ጠቅሰው፤ በፕሮግራሙ ለታቀፉ ዜጎች  የአቅም ግንባታና በቁጠባ ዙሪያ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ዋና  ዳይሬክተር አቶ አንዷለም ጤናው በበኩላቸው፤ የትብብር መድረኩ ከተሞች የእርስ በርስ  ግኑኙነታቸውን እንዲያጠናክሩና ልምድ እንዲለዋወጡ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ ከተሞች በገቢ ራሳቸውን እንዲችሉና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ስራ አጥነትን እንዲቀንሱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰሩ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የትብብር መድረኩ በሀገሪቱ 108 ከተሞች በአባልነት ያቀፈ ነው ያሉት አቶ አንዷለም፤  በከተሞች የአካታችን፣ስትራቴጂና የልማት ፕሮግራሞች አካል ጉዳተኞችን ባመከለ መልኩ እንዲከናወን በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም