የልማት ድርጅቶች ትርፋማነትን ከህዝብ አገልግሎት ጋር ማጣጣም አለባቸው - ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
የልማት ድርጅቶች ትርፋማነትን ከህዝብ አገልግሎት ጋር ማጣጣም አለባቸው - ቋሚ ኮሚቴው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 15/2017(ኢዜአ)፦ የልማት ድርጅቶች ትርፋማነትን ከህዝብ አገልግሎት ጋር አጣጥመው ማስኬድ እንደሚገባቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት የልማት ድርጅት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
ቋሚ ኮሚቴው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የስምንት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ገምግሟል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ፕሮፌሰሬ መሀመድ አብዶ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሀገር ውስጥ ተኪ ግብዓትን በመጠቀም የበለጠ ትርፋማና ውጤታማ እንዲሆኑ መደገፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የልማት ድርጅቶች ከተቋቋሙለት ተልዕኮ አንፃር ትርፋማና ውጤታማነታቸውን አጣጥሞ በማስኬድ የተጀማመሩ ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።
ግዢ፣ ተሰብሳቢ ሂሳቦችን በወቅቱ መሰብሰብና ተያያዥ የፋይናንስ እንቅስቃሴዎችን እንዲሁም በወቅቱ ሂሳብ የማወራረድ ስራ ትኩረት እንደሚያሻቸው አስገንዝበዋል።
ድርጅቶች የገቢ ለውጥ በማምጣት ትርፋማና ውጤታማ አገልግሎት ለህዝቡ እንዲሰጡ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ስለሺ ኮሬ(ዶ/ር) በበኩላቸው የመንግስት ትርፍ ድርሻን በጊዜው ለማሳወቅ የተከናወነው ስራ እና የድርጅቶች ቅንጅታዊ አሰራርን በጥንካሬ አንስተዋል።
ተቋሙ ከተቋቋመለት ተልዕኮ አንፃር የመንግስት የልማት ድርጅቶች የህዝብ አገልግሎትንና ትርፋማነትን አብሮ ማስኬድ እንዳለባቸው ገልፀው ለዚህም አሰራር ሊበጅለት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ስራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ(ዶ/ር) የኮርፖሬት አስተዳደሬ ስርዓትን ከአዲሱ የልማት ድርጅቶች አዋጅ ጋር በማጣጣም ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በግማሽ አመቱ 901 ቢሊዮን ብር ገቢ ማመንጨት መቻሉንና 6 ነጥብ 7 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር መገኘቱን ጠቁመዋል።
14 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የመንግስት ትርፍ ድርሻ ለገንዘብ ሚኒስቴር ገቢ መደረጉንም በሪፖርታቸው አመልክተዋል።
በውይይቱ የፕሮጀክቶች ዋጋ ተለዋዋጭነት፣ የረጅም ጊዜ ተሰብሳቢዎች፣ ከመሬት ጋር ተያይዞ ያለ የመጠቀም መብት ብሎም የኦዲት ሪፖርቶችንና ሌሎች መረጃዎችን በድረ ገፅ ለህዝብ ይፋ አለማድረግን እንደ ተግዳሮት ተነስተዋል፡፡
በቀጣይም የውጭ ምንዛሪ፣ ግብአት እጥረትን ለመቅረፍ እንዲሁም ለዲጂታላይዜሽንና ፈጠራ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ መግለጻቸውን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።