የሂሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት መቋቋም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ያስችላል - የዘርፉ ባለሙያዎች - ኢዜአ አማርኛ
የሂሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት መቋቋም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ያስችላል - የዘርፉ ባለሙያዎች
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 15/2017(ኢዜአ)፡- የሂሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት መቋቋም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና አለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ገለፁ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 19ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ በሙሉ ድምጽ ማፅደቁ ይታወሳል።
የኢንትስቲትዩቱ መቋቋም በኢትዮጵያ ብቁና ተወዳዳሪ የሂሳብ ባለሙያዎችን ለማፍራትና የኢኮኖሚ እድገትን ዘላቂነት ማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ተናግረዋል።
የውጭ ኦዲተሮች ማህበር ፕሬዝዳንት ዳንኤል ጌታነህ ለኢዜአ እንዳሉት ኢንስቲትዩቱ ለባለሙያዎች ተከታታይ የሙያ ማጎልበቻ ስልጠና የሚሰጥና በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው እውቅና እንዲያገኙ የሚያስችል ነው።
ኢንስቲትዩቱ የአለም አቀፍ የሂሳብ ባለሙያዎች ፌዴሬሽን(IFAC) አባል በመሆን መስራቱ ባለሙያዎች አዳዲስ አለም አቀፍ አሰራሮችን በየጊዜው እንዲገነዘቡ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር እንደሆነም ተናግረዋል።
ይህም የሂሳብ ባለሙያዎች ወቅታዊ ሁኔታዎችን በየጊዜው እንዲረዱ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመው በኢትዮጵያ ብቁ የሂሳብ ባለሙያዎችን ማፍራት የሚያስችል ነው ብለዋል።
የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት በብቁ የሂሳብ ባለሙያዎች መመራቱ የኢኮኖሚ እድገትና ዘላቂነትን የሚያረጋግጥ እንደሆነም ተናግረዋል።
ታክስ የመሰብሰብ አቅምን የሚያሳድግና የፋይናንስ አስተዳደሩ በብቁ ባለሙያዎች እንዲመራ የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል።
ስርቆትና ማጭበርበርን ለማስቀረት እንዲሁም ግልፅነትና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ይረዳልም ነው ያሉት።
ኢንቨስተሮችና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ብሎም አለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ አስተዋፅኦ ያለው መሆኑንም ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር ፍቃዱ አጎናፍር በበኩላቸው የኢንስቲትዩቱ መቋቋም የሂሳብና ኦዲት ባለሙያዎችና የፋይናንስ ሪፖርት ጥራት ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር መፍታት የሚያስችል ነው ብለዋል።
ብቁ የሂሳብ ባለሙያዎች ማፍራት ለካፒታል ገበያ ስርዓቱ እንዲሁም በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠናና በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን ብሎም በአጀንዳ 2063 የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት የሚያግዝ እንደሆነም ተናግረዋል።
ኢንስቲትዩቱን ስራ ለማስጀመር የስትራቴጂክ እቅድና የፋይናንስ ምንጩን የተመለከቱ ሰነዶች እንዲሁም የድርጊት መርሃ ግብር መዘጋጀቱን ገልፀዋል።