የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) ከአልጄሪያ የኢነርጂ፣ማዕድንና ታዳሽ ኃይል ሚኒስትር ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) ከአልጄሪያ የኢነርጂ፣ማዕድንና ታዳሽ ኃይል ሚኒስትር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፤መጋቢት 15/2017 (ኢዜአ)፦የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) በአልጄሪያ የኢነርጂ፣ ማዕድንና ታዳሽ ኃይል ሚኒስትር መሐመድ አርካብ ከተመራ ልዑክ ጋር ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር)፥ ከሚኒስትሩ ጋር በሁለቱ ሃገራት የንግድና የኢነርጂ አስተዳደር ትብብር ዙሪያ ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያና አልጄሪያ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው ሃገራት መሆናቸውን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሃገራት ጋር የንግድ ግንኙነት ለማስፋት ያላትን ቁርጠኝነትና በዚህ ረገድ እየተሰራ ያለውን ተግባር አስመልክቶ ለሚኒስትሩ ማብራሪያ መስጠታቸውን ጠቁመዋል።
ከአልጄሪያ ጋር ያለውን የንግድ ትስስር ለማጠናከር በሚቻልባቸው አግባቦች ዙሪያ ገንቢ ውይይት ማድረጋቸውን ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።
አልጄሪያ በኢነርጂ ልማትና አስተዳደር የዳበረ ልምድ አላት ያሉት ሚኒስትሩ፥በዚህ ረገድ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለሚከናወኑ ስራዎች አጋዥ የሚሆኑ የቴክኒክና የስልጠና ልውውጦችን ለማድረግ ከስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል።
ልዑካን ቡድኑ ኢትዮጵያ ባካሄደችው ሪፎርምና በተገኙ ተጨባጭ ውጤቶች ያላቸውን አድናቆትም መግለጻቸውንም ተናግረዋል።