መንግስት ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር እየሄደበት ያለው የዲፕሎማሲ መንገድ የሚደገፍ ነው-የጂንካ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር እየሄደበት ያለው የዲፕሎማሲ መንገድ የሚደገፍ ነው-የጂንካ ከተማ ነዋሪዎች
ጂንካ፤መጋቢት 14/2017 (ኢዜአ)፦መንግስት ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሰጥቶ መቀበል መርህ በትብብር በመስራት ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር እየሄደበት ያለው የዲፕሎማሲ መንገድ የሚደገፍና መጠናከር ያለበት ነው ሲሉ የጂንካ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢያ አሕመድ (ዶ/ር)፥ሰሞኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስትን ግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ከምክር ቤቱ አበላት ለቀረቡላቸው የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል።
በዚህም መንግስት በሰጥቶ መቀበል መርህ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመልካም ግንኙነት ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር በትብብር እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የጂንካ ከተማ ነዋሪዎችም መንግስት ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለንን የረጅም ዓመታት ወዳጅነት በማጠናከር በሰጥቶ መቀበል መርህ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ እየሄደበት ያለው መንገድ የሚበረታታና የሚደገፍ መሆኑን ገልጸዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል መምህር ወንድሙ ግርማ፥ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማብራሪያ በአግባቡ መከታተላቸውን ጠቅሰው፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽና ማብራሪያ የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያጤነና ጊዜውን የዋጀ ሆኖ እንዳገኙት ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ካነሷቸው ሀሳቦች መካከል ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ የሀገሪቱን የባህር በር የማግኘት ጥረት ለማሳካት መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ መገንዘባቸውን ገልጸዋል።
ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ጉዳይ በቀላሉ የሚታይና ለመንግስት ብቻ መተው እንደሌለበት ጠቁመው፥መንግስት በሰጥቶ መቀበል መርህ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትበብር በመስራት የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር እያደረገ ያለው ዲፕሎማሲያዊ ጥረትን አድንቀዋል።
ይህን የመንግስት ጥረት ሁላችንም መደገፍና ማገዝ አለብን ያሉት መምህር ወንድሙ፥ ከቀጠናው ተለዋዋጭ ባህሪይ አኳያ መንግስት ጉዳዩ በጥንቃቄ ለማስኬድ የጀመረው ጥረት መጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ቶማስ ጠልታ በበኩላቸው እንዳሉት፥መንግስት የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር የሚከተለው የሰጥቶ መቀበል መርህ የሚደገፍና የሚበረታታ ነው።
የባህር በር ለኢትዮጵያና ለህዝቦቿ የሚኖረውን ጥቅም ከግምት በማስገባት የተጀመረው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
በተለይ ምሁራን በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን ሀሳቦች በማንሸራሸርና የባህር በር ከማግኘት መብት ጋር የተያያዙ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን ጭምር ጠቅሰው፥ በመሞገት የመንግስትን ጥረት ማገዝ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ባህር በር የማግኘት ጥያቄ ቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑን ያነሱት ድግሞ አቶ አሊ ሙሐመድ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ናቸው።
የባህር በር አለመኖር በተለይ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ የጎላ ጫና ሲያሳድር መቆየቱን አስታውሰው፥ይህንን ችግር ለመፍታትና ብሔራዊ ጥቅምን ለማሳደግ መንግስት እየተከተለ ያለው ዲፕሎማሲያዊ መንገድ መጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በተለያዩ አካላት ተቀባይነት ያገኘበት ሁኔታ እንዳለ ያነሱበት መንገድ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት ከአጎራባች ሀገራት ጋር ለጋራ ተጠቃሚነት የጀመራቸው ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እንደዜጋ ሁላችንም ማገዝ ይኖርብናል ብለዋል።