ቀጥታ፡

በባሕር በር ጉዳይ የመንግስት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የሚደነቅ ነው- የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች

ጎንደር፤ መጋቢት 13/2017 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ ዓለም አቀፍ አጀንዳ በማድረግ ረገድ የመንግስት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተለይም በባሕር በር ጉዳይ ላይ የሰጡትን ማብራሪያ በተመለከተ የኢዜአ ሪፖርተር በጎንደር ከተማ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን አነጋግሯል።

የዋሪዎቹ እንዳሉት በኢትዮጵያ የባሕር በርን ጉዳይ የህዝብ ፍላጎት የነበረ ቢሆንም በነበረው ፖለቲካ እንደ ጥፋትና ነውር በመቁጠር ታፍኖ የኖረ የህዝብ ጥያቄ ነው።

ይህንን ሁሉ የዘመናት ዝምታ በመስበር የባሕር በር ጉዳይ የኢትዮጵያ የአደባባይ አጀንዳ ለተደረገበት መንገድ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የላቀ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

ከጎንደር ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ቸርነት መንግስቴ፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር ያጣችበት ሁኔታ ሀገርና ህዝብን የጎዳ ስብራት ሆኖ በዝምታ ታፍኖ የኖረ ጉዳይ መሆኑን አስታውሰዋል።

አሁን ላይ መንግስት በህጋዊ፣ በሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የባሕር በር የማግኘትን ጥያቄ ማንሳቱ የገቢ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የላቀ ጥረት የሚደነቅ መሆኑን በማንሳት ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከሀገርም ባለፈ ዓለም አቀፍ ጉዳይ በማድረግ ረገድ መንግስት ያደረገውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አድንቀዋል።

የባሕር በር ጥያቄው በየትኛውም መመዘኛ ትክክል በመሆኑ የመንግስትን ጥረት በማገዝ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት ነው ያሉት።

ወጣት ዳንኤል ሙሉጌታ እና ችሎት አዳነ፤ የባሕር በር ጉዳይ በፓርላማ አጀንዳ ሆኖ መቅረቡ ተገቢና ወቅቱን የዋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

ለጥያቄው ምላሽና ለዓላማው መሳካት ሁላችንም የበኩላችንን ሚና መወጣት አለብን ነው ያሉት።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢንሼቲቭ የተከናወኑ የከተማ ልማት ስራዎች ትልቅ ተስፋ የተሰነቀባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም