የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የጀመረው በቴክኖሎጂ የተደገፈ የክፍያ ስርዓት ቀልጣፋ አገልግሎት እንድናገኝ እያስቻለን ነው - ተጠቃሚዎች - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የጀመረው በቴክኖሎጂ የተደገፈ የክፍያ ስርዓት ቀልጣፋ አገልግሎት እንድናገኝ እያስቻለን ነው - ተጠቃሚዎች

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 13/2017(ኢዜአ)፡- የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የጀመረው በቴክኖሎጂ የተደገፈ የክፍያ ስርዓት ቀልጣፋ እና ዘመናዊ አገልግሎት እንድናገኝ አስችሎናል ሲሉ የባቡር ትራንስፖርት ተጠቃሚዎች ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት በተመረጡ የባቡር ጣቢያዎች የዲጂታል ትኬት አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡
ከዲጂታል ትኬት አገልግሎት ተጠቃሚዎች መካከል ወጣት መብራቴ ደረጀ ለኢዜአ እንዳለው፤ ዲጂታል የክፍያ ሥርዓት ተግባራዊ መደረጉ ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘት አስችሏል፡፡
የዲጂታል የክፍያ ሥርዓት እንግልትን የሚያስቀርና ጊዜውን የዋጀ አገልግሎት መሆኑን ገልፆ፤ አሰራሩን ሙሉ በመሉ ለመተግበር ለማህበረሰቡ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ ተናግሯል።
የዲጂታል የክፍያ ሥርዓት ጊዜን በመቆጠብ ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት መሥጠት የሚያስችል በመሆኑ በሁሉም አካባቢዎች ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የገለጸው ደግሞ መምህር ዮርዳኖስ ወልደአማኑኤል ነው፡፡
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ወጣት ኪሶ ጋሩማ አገልግሎቱ በአንድ ትኬት ከሁለት ጊዜ በላይ የሚጠቀሙ ሰዎችን በማስቆም ብልሹ አሰራርን መቆጣጠር ያስችላዋል ብሏል፡፡
የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ብርሃነ አበባው(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የባቡር ትራንስፖርት የትኬት አገልግሎት በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ የሙከራ ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
የወረቀት ትኬት ስርዓት የመዲናዋን የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት የማይመጥን መሆኑን ገልጸው፤ ስርዓቱ የተሳለጠ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችልም ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር በ19 ባቡሮች ለህብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ 21 ለማድረስ እቅድ ተይዟል ብለዋል፡፡