ሀገራዊ ግዳጅ በብቃት ለመወጣት ዝግጁ ነን - ተመራቂ የሜካናይዝድ ሙያተኞች

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 13/2017(ኢዜአ)፡-የሚሰጣቸውን ሀገራዊ ግዳጅ በብቃት መወጣት የሚያስችል ወታደራዊ ዕውቀትና ክህሎት ማግኘታቸውን በመከላከያ ትምህርትና ስልጠና መምሪያ የአዋሽ ዓርባ የውጊያ ቴክኒክ ትምህርት ቤት የሜካናይዝድ ሙያተኛ ምሩቃን ገለጹ።

በመከላከያ ትምህርትና ስልጠና መምሪያ የአዋሽ ዓርባ የውጊያ ቴክኒክ ትምህርት ቤት በወታደራዊ ሜካናይዝድ ትምህርት ያሰለጠናቸውን ሙያተኞች አስመርቋል።

የትምህርት ቤቱ ሜካናይዝድ ተመራቂ መሰረታዊ ወታደር ማስተዋል ማቴዎስ፤ በውጊያ ቴክኒክ ትምህርት ቤቱ የስልጠና ቆይታቸው ግዳጅን በብቃት መወጣት የሚያስችል ወታደራዊ እውቀትና ክህሎት ማግኘታቸውን ገልጿል።

የትምህርት ቤቱ ሜካናይዝድ ተመራቂ ምክትል አስር አለቃ አብዱላዚዝ መሀመድ፤ የትምህርት ቤቱ አሰልጣኞች ተገቢውን ወታደራዊ ትምህርትና ስልጠና በመስጠት ለምርቃት እንዳበቋቸው አንስቷል።


 

እንስቷ የሜካናይዝድ ተመራቂ መሰረታዊ ወታደር መቅደስ ንጋቱ፤ በቆይታቸው የአካል ብቃት፣ የሥነ-ልቦና፣ የሰልፍና ቴክኒክ ዕውቀትና ክህሎት መሰነቃቸውን ተናግራለች። 


 

ሌላኛው የትምህርት ቤቱ ሜካናይዝድ ተመራቂ መቶ አለቃ አቦሀይ ቸኮለ፤ መንግስት የሚሰጣቸውን የትኛውንም አይነት ግዳጅ በብቃት መወጣት የሚያስችል ስልጠና ወስደናል ብሏል።


 

በቀጣይ ለኢትዮጵያ ዳር ድንበር መከበር መንግስት የሚሰጣቸውን ግዳጅ በብቃት ለመወጣት መዘጋጀታቸውን የገለጸው ደግሞ ተመራቂ ሀምሳ አለቃ ታዘብ ጥጋቡ ነው።


 

የትምህርት ቤቱ አሰልጣኝ ሌተናል ኮሎኔል ዮናስ አየለ እንደገለጹት፤ ትምህርት ቤቱ ባለፉት አርባ ሰባት ዓመታት የሀገር አለኝታ የሆኑ ወታደራዊ ሙያተኞችን ሲያፈራ መቆየቱን አስታውሰዋል።



ለምርቃት የበቁት ወታደራዊ የሜካናይዝድ ሙያተኛ ሰልጣኞቹ የሚሰጣቸውን ግዳጅ በብቃት መወጣት የሚያስችል የቴክኒክና የሥነ-ልቦና አቅም ተፈጥሮላቸዋል ብለዋል።


 

ሌላኛው የትምህርት ቤቱ አሰልጣኝ መቶ አለቃ አብሽሩ ዓለሙ፤ ምሩቃኑ በትምህርት ቆይታቸው ግዳጅን በብቃት በመወጣት የሀገርን ሉዓላዊ ክብር መጠበቅ የሚያስችል የንድፈ ሃሳብና የተግባር ስልጠናቸውን በሚገባ እንደተከታተሉ ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም