ስፖርታዊ ውድድሮች የህዝቦችን የእርስ በርስ ትስስርና አንድነት በማጠናከር ረገድ ፋይዳቸው የጎላ ነው - አቶ ኢሳያስ ጅራ - ኢዜአ አማርኛ
ስፖርታዊ ውድድሮች የህዝቦችን የእርስ በርስ ትስስርና አንድነት በማጠናከር ረገድ ፋይዳቸው የጎላ ነው - አቶ ኢሳያስ ጅራ
ጎንደር ፤መጋቢት 13/2017 (ኢዜአ) ፡- ስፖርታዊ ውድድሮች የህዝቦችን የእርስ በርስ ትስስርና አንድነት በማጠናከር ረገድ ፋይዳቸው የጎላ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ገለጹ፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲና ሆስፒታል የምስረታ በዓልን አስመልክቶ በቅዱስ ጊዮርጊስና በፋሲል ከነማ የእግር ኳስ ክለቦች መካከል የተካሄደው የእግር ኳስ ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቆ ክለቡ የተዘጋጀውን ዋንጫ ወስዷል።
ፕሬዚዳንቱ አቶ ኢሳይያስ ጅራ በውድድሩ መክፈቻ ላይ እንደገለጹት የእግር ኳስ ጨዋታ በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ እጅግ ተወዳጅና ዘመን ተሻጋሪ ታሪክ ያለው ነው።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲም የምስረታ በዓሉን በማስመልከት ይህን ታሪካዊ የወዳጅነት የእግር ኳስ ውድድር በማካሄዱ ምስጋና አቅርበው ይህም ዩኒቨርሲቲው ለስፖርት ልማት የሰጠው ትኩረት ማሳያ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ደማቅ ታሪክን የጻፈው መንግስቱ ወርቁ ለብሶት ይጫወት የነበረውን "8 ቁጥር ማልያ" የመታሰቢያ ፎቶ ለጎንደር ዩኒቨርሲቲና ለከተማ አስተዳደሩ በስጦታ አበርክተዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን በበኩላቸው የፋሲል ከነማና የቅዱስ ጊዮርጊስ የእግር ኳስ ስፖርት ክለቦች በአገራችን እግር ኳስ ታሪክ አንጋፋ ክለቦች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በጎንደር ከተማ ደረጃውን የጠበቀ የእግር ኳስ ሜዳ እንዲገነባ ዩኒቨርሲቲው ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ጠቁመው ሁለቱ ክለቦች የተደረገላቸውን ጥሪ በመቀበል የወዳጅነት ጨዋታ በማካሄዳቸው ምስጋና አቅርበዋል፡፡
"በቀጣይም የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ በራሱ ሜዳ የሚጫወትበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ከተማ አስተዳደሩ በትኩረት እየሰራ ነው" ያሉት ደግሞ በምክትል ከንቲባ ማእረግ የከተማው ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ልጃለም ግርማይ ናቸው፡፡
በዚህም የፋሲለደስ ስታዲየም የሀገራችንን ታላላቅ የእግር ኳስ ክለቦችን ማስተናገድ እንዲችል ደረጃውን በጠበቀ መንገድ ጠግኖ ወደ ስራ ለማስገባትም ከተማ አስተዳደሩ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው 70ኛ ዓመትና የሆስፒታሉ 100ኛ ዓመት ምስረታን ምክንያት በማድረግ በተካሄደው ውድድር የሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች፣ የከተማ አስተዳደሩና የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ተገኝተዋል።