ቀጥታ፡

ኢንስቲትዩቱ የሰጠን የሙያ ስልጠና በስራችን ውጤታማ እንድንሆን አስችሎናል - ኢንተርፕርነሮች

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 13/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ኢንተርፕርነር ልማት ኢንስቲትዩት የሰጣቸው የሙያ ስልጠና በስራቸው ውጤታማ እንዳደረጋቸው ኢዜአ ያነጋገራቸው ኢንተርፕርነሮች ገለፁ።

ባለፉት 8 ወራት ከ11 ሺህ በላይ አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች ወደ ስራ መግባታቸውን የኢንተርፕራይዝ ልማት ኢንስቲትዩት ገልጿል።

ኢንስቲትዩቱ ካሰለጠናቸው ሰልጣኞች መካከል ሓጉሽ ተኽላይ ለኢዜአ እንደገለጸችው የተሰጣቸው ሙያዊ ስልጠና በስራዋ ውጤት አስገኝቶላታል።

ስልጠናው አካባቢዋን በአግባቡ ተገንዝባ በስራ ላይ የሚገጥሟትን ፈተናዎች በቀላሉ ማለፍ እንድትችል ግንዛቤ የፈጠረላት መሆኑንም ነው የጠቀሰችው።

በኢንስቲትዩቱ የተሰጠው ስልጠናም የስራና የፈጠራ ግንዛቤዋ ማደጉን ትገልፃለች።

በአነስተኛ ካፒታል በቡና ጠጡ የጀመረችው ስራ አሁን ምግብና መጠጥን ጨምሮ በተሻለ ደረጃ መስፋቱን የገለፀችው ኢንተርፕርነር ደግሞ ሂሩት ተረፈ ናት።

ቀደም ሲል የቤቷንና የስራ ቦታዋን ወጪና ገቢ አንድ ላይ ትጠቀም እንደነበር አስታውሳ፣ በኢንስቲትዩቱ ባገኘችው ስልጠና የገንዘብ አያያዝና አጠቃቀሟ መሻሻሉንም ገልፃለች።

ኢንተርፕርነሮቹ በአሁን ወቅት ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም የስራ ዕድል መፍጠራቸውን ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕርነር ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሀሰን ሁሴን(ዶ/ር) ኢንስቲትዩቱ ስራ ፈጠራ ላይ ያተኮሩ አጫጭርና ረጃጅም ስልጠናዎችን እየሰጠ ነው ብለዋል።

የፈጠራ ሀሳብ ያላቸው ወጣቶች ወደ ስራ መግባት የሚያስችላቸውን የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያገኙ እገዛ እንደሚያደርግም ነው የተናገሩት።

በተያዘው በጀት ዓመት ስምንት ወራት የፈጠራ ሀሳብ ላላቸው ወጣቶች የተለያዩ የሙያ ስልጠናዎች መሰጠቱንም ገልጸዋል።

በዚህም ከ11ሺህ በላይ አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች ወደ ስራ መግባታቸውንና በዚህም ለ160 ሺህ ወጣቶች የስራ ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል።

ግብርና፣ ቴክኖሎጂ፣ ቱሪዝም፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ምግብና መጠጥ እንዲሁም የጤና አገልግሎት ኢንተርፕራይዞቹ ከተሰማሩባቸው ዘርፎች ውስጥ ይጠቀሳሉ ብለዋል።

ኢንተርፕራዞችን አደራጅቶ በማጠናከር ዜጎች የስራ ዕድል እንዲያገኙ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈርሃት ካሚል መግለፃቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም