በወልዲያ -ቆቦ መንገድ ላይ ተሰብሮ የቆየው የብረት ድልድይ በሌላ አዲስ ተተክቶ ዛሬ አገልግሎት መስጠት ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በወልዲያ -ቆቦ መንገድ ላይ ተሰብሮ የቆየው የብረት ድልድይ በሌላ አዲስ ተተክቶ ዛሬ አገልግሎት መስጠት ጀመረ
ወልዲያ፤ መጋቢት 13/3017(ኢዜአ)፡- በወልዲያ-ቆቦ መንገድ ላይ ተሰብሮ የቆየው የአሚድ ወንዝ የብረት ድልድይ በሌላ አዲስ ተተክቶ ዛሬ ከሰአት በኋላ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ።
በአስተዳደሩ የድልድዮችና ስትራክቸር ዳይሬክተር ኢንጂነር ተክለስላሴ ንዳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የአሚድ ወንዝ የብረት ድልድይ ከክብደት በላይ በጫነ ተሽከርካሪ ምክንያት የመሰበር ጉዳት ደርሶበት ቆይቷል።
ይህን ችግር ለመፍታት ቅድሚያ ተሰብሮ የወደቀውን ድልድይ ለማንሳት በማዳገቱ የተለያዩ ከባድ ማሽነሪዎችንና ሌሎች አጋዥ መሳሪያዎችን በመጠቀም ቦታዎችን ለማጽዳት ጊዜ እንደወሰደ ተናግረዋል።
ይህም ሆኖ ቀድሞ ከነበረው በጣም የተሻለና ጠንካራ አዲስ የብረት ድልድይ በማስቀመጥ ተተክቶ ለአገልግሎት ማብቃት መቻሉን አስታውቀዋል።
በአዲስ የተተካው የብረት ድልድይ ርዝመት 45 ነጥብ 7 ሜትርና ስፋቱ ደግሞ 4ነጥብ 2 ሜትር መሆኑን ጠቅሰዋል።
በሥራውም በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የድልድዮችና ስትራክቸር ዳይሬክቶሬት እና በአስተዳደሩ የኮምቦልቻ ቅርንጫፍ እንደተሳተፉ ተናግረዋል።
ለአንድ ወር ተኩል ያህል በተለዋጭ ስንሄድበት የነበረው ድልድይ በአዲስ ተሰርቶ ለአገልግሎት መብቃቱ በጣም አስደስቶናል "ያሉት አሽከርካሪ አዲሱ አጥናፉ ናቸው።
ድልድዩ በዚህ ፍጥነት ይሠራል የሚል ግምት አልበረኝም ያሉት ደግሞ ሌላው አሽከርካሪ አቶ አስማረ ሲሳይ ናቸው።
መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ለአገልግሎት እንዲበቃ ማድረጉ በጣም ተደስተናል፤ እናመሠግናለም ብለዋል
የአሚድ ወንዝ ከወልዲያ ከተማ በ35 ኪሎሜትር የሚርቅ ሲሆን፣የካቲት 28 / 2017 ዓ .ም ከባድ ጭነት በጫነ ተሽከርካሪ ምክንያት ተደርምሶ በሌላ ለመተካት እየተሰራ እንደሆነ መዘገባችን የሚታወስ ነው።
በድልድዩ መሰበር ምክንያት የትራንሰፖርት አገልግሎት እንዳይስተጓጎል ጊዜያዊ መፍትሄ ለመስጠት ተለዋጭ መተላለፊያ መንገድ መሰራቱን በወቅቱ ተገልጿል።