ቀጥታ፡

መንግሥት እና የግሉ ዘርፍ በአረንጓዴ ትራንስፖርት በጋራ የሚሰሩበት የአሰራር ማዕቀፍ ወደ ስራ ገብቷል - ሚኒስቴሩ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 13/2017(ኢዜአ)፦ መንግሥት እና የግሉ ዘርፍ በአረንጓዴ ትራንስፖርት በጋራ የሚሰሩበት ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሀሰን ገለጹ።

ሚኒስትር ዴኤታው ከግራንቪል ኢነርጂ ዋና ስራ አስፈጻሚ ታቢ ቲ ታቢ ጋር ተወያይተዋል።

ውይይታቸው ያተኮረው በአረንጓዴ ትራንስፖርት በተለይም በኤሌክትሪክና በፀሐይ ኃይል በሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ላይ በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው።

ሚኒስትር ዴኤታው በሀገር አቀፍ የተጀመረውን የአረንጓዴ ትራንስፖርት የማስፋት ስራ ለማሳካት የመንግስትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ስራዎችን የሚደግፉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተዘጋጅተው ወደ ስራ መግባታቸውን ገልጸዋል።

መንግስት በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎት ካላቸው አካላት ጋር በትብብር መስራት እንደሚፈልግም ተናግረዋል።

በዚህ ረገድም መንግስት ለድርጅቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የግራንቪል ኢነርጂ ዋና ስራ አስፈፃሚ ታቢ ቲ ታቢ ድርጅቱ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ፅህፈት ቤቶች እንዳሉት ገልጸው ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ትራንስፖርት ያላትን እምቅ አቅም ከግምት በማስገባት ጽህፈት ለመክፈት እና ስራ ለመጀመር ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል።

በውይይቱ ላይ ግራንቪል ኢነርጂ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ኃይል መሙያ ማዕከላት ግንባታና ባትሪ ምርት ላይም ለመሠማራት እንደሚሻ መግለጹን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም