በሪፎርሙ በወንጀል መከላከልም ሆነ በወንጀል ምርመራ ብቁ ሆኖ ለመገኘት እንደተቋም ትላልቅ ሥራዎችን ስንሰራ ቆይተን አስደናቂ ውጤቶችን አስመዝግበናል - ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግሥቴ - ኢዜአ አማርኛ
በሪፎርሙ በወንጀል መከላከልም ሆነ በወንጀል ምርመራ ብቁ ሆኖ ለመገኘት እንደተቋም ትላልቅ ሥራዎችን ስንሰራ ቆይተን አስደናቂ ውጤቶችን አስመዝግበናል - ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግሥቴ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 13/2017(ኢዜአ)፡- በሪፎርሙ በወንጀል መከላከልም ሆነ በወንጀል ምርመራ ብቁ ሆኖ ለመገኘት እንደተቋም ትላልቅ ሥራዎችን ስንሰራ ቆይተን አስደናቂ ውጤቶችን አስመዝግበናል ሲሉ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግሥቴ ገለጹ።
ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ ይህን ያሉት የክልልና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ኃላፊዎች የሚሳተፉበትን 19ኛው የኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሚሽነሮች ጉባኤን በከፈቱበት ወቅት ነው።
በጉባኤው ሀገርን በጋራ ለማፅናት እና የህዝብን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ የሚያስችል የጋራ መግባቢያ ሰነድ በተፈራረምነው መሠረት በቀጣይ በቅንጅትና በመደጋገፍ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የሰብአዊ መብት አያያዝን በማጠናከር ሀገራዊ ራዕይን ለማሳካት ሁሉም መረባረብ አለበት ብለዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሕገ-መንግሥቱንና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን እንዲሁም ሌሎች ሕጎችን በማክበርና በማስከበር ሕብረተሰቡን በወንጀል መከላከልና ምርመራ በማሳተፍ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት እየጠበቀ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ጉባኤው ማንኛውም የወንጀል ተጠርጣሪ የትኛውም ክልል ተደብቆ ማምለጥ በማይችልበት ሁኔታ ላይ በመወያየትና በአፈፃፀሙ ላይ ስምምነት ላይ በመድረስ ሀገራችን በግብርና፤ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም እና በቴክኖሎጂ የጀመረችውን የኢኮኖሚ ሪፎርም ግቡን እንዲመታ የፀጥታ ዘርፉ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል
በመሆኑም በወንጀል መከላከልም ሆነ በወንጀል ምርመራ አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገብ ይኖርብናል ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ።
ከጉባኤው ተሳታፊዎች ለቀረቡ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽ ሰጥተው በማጠቃለያቸው የፖሊስ ስታንዳርድ ማስጠበቅ የክልል ፖሊስ ስልጣንን መጋፋት እንዳልሆነ አብራርተዋል።
የተወሰደው ልምድና ተሞክሮ በቀጣይ ለሚሠሩ የምርመራ ሥራዎች መጠናከር ከፍተኛ አበርክቶ ስላለው ከዚህ በኋላ በምርመራ ሥራ ረገድ ጉራማይሌ አሠራር እንደማይኖርም ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 720/2004 አንቀጽ 18 ንዑስ አንቀጽ 3 ሥር ከተዘረዘሩት የፌደራል፣ የክልል እና የከተማ አስተዳደር ፖሊስ ግንኙነቶች አንዱ የወንጀል ምርመራ ሥራዎችን በቅንጅትና በመደጋገፍ የሚሠሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት መሆኑን በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሥልጣንና ተግባር እንደተደነገገም በውይይቱ መነሳቱን በፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ባለፉት ዓመታት በአንዳንድ አካባቢዎች ሲስተዋሉ የነበሩ ግጭቶችና የሽብር ወንጀሎች፣ ከባድና ውስብስብ የሙስና እና የኢኮኖሚ ወንጀሎች፣ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ምርመራ ላይ ባስመዘገብነው ውጤት የፌደራልና የክልል መንግሥታት የሥራ ኃላፊዎች፣ የፀጥታና የደኅንነት አካላት፣ ባለድርሻ እና አጋር አካላት እንዲሁም ከፖሊስ ጎን ተሰልፎ የዜግነት ኃላፊነቱን እየተወጣ ለሚገኘው ኅብረተሰብ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግሥቴ ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።