የክልሉ ህዝብ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ቀሪ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉ ህዝብ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ቀሪ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ተጠየቀ
አርባምንጭ ፤መጋቢት 13/2017(ኢዜአ):- የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ቀሪ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ እንዲያጠናክር የክልሉ አፈ-ጉባኤ አለማየሁ ባውዲ ጥሪ አቀረቡ።
ዓለም አቀፍ የውሃ ቀን በዓልና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ አቀባበል ስነ-ስርዓት በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሄዷል።
በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አፈ-ጉባኤ አለማየሁ ባውዲ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ቀሪ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ የክልሉ ህዝብ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።
ብሔራዊ ኩራታችን የሆነውን ህዳሴ ግድብ ለማጠናቀቅ ህዝቡን በማስተባበር ከተሰጠን በላይ እንሠራለን ብለዋል።
ግድቡ የሀገራችን ብልጽግና ማረጋገጫ ነው ያሉት አፈ-ጉባኤው የአሁኑ ትውልድ ድህነትን በማሸነፍ የራሱን ታሪክ ሊጽፍ ይገባል ብለዋል።
የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምስ አድማሱ (ዶ/ር) በበኩላቸው የዞኑ ህዝብ ከዚህ ቀደም ለግድቡ ግንባታ ከ301 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን አውስተዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም ከታቀደው 130 ሚሊዮን ብር እስካሁን 60 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን በቀሪ ወራት ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ከህዝቡ ጋር እንሠራለን ብለዋል።
ለዚሁ ስኬት የዞኑ ባለሀብቶች፣ የመንግስት ሠራተኞች፣ ነጋዴዎች፣ አርሶ አደሮች፣ ሴቶች፣ ወጣቶችና ሌሎችም የበኩላቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱም ጥሪ አቅርበዋል።