የህዳሴው ግድብ ግንባታ የይቻላል መንፈስ መገለጫችንና በመተባበር የኢትዮጵያን የልማት ህልሞች ማሳካት እንደሚቻል ማሳያ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴው ግድብ ግንባታ የይቻላል መንፈስ መገለጫችንና በመተባበር የኢትዮጵያን የልማት ህልሞች ማሳካት እንደሚቻል ማሳያ ነው
ቦንጋ/ ጋምቤላ ፤ መጋቢት 13/2017 (ኢዜአ) :-ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የይቻላል መንፈስ መገለጫችንና በመተባበር የኢትዮጵያን የልማት ህልሞች ሁሉ ማሳካት እንደሚቻል ማሳያ ነው ሲሉ በቦንጋ እና ጋምቤላ ከተሞች ነዋሪዎች ገለጹ።
ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መጋቢት 11/2017ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመገኘት ከአባላቱ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል።
በማብራሪያቸውም ለመላው አፍሪካ ኩራትና የይቻላል መንፈስ ያጎናጸፈው የህዳሴ ግድብ ቀሪ ስራዎች በማጠናቀቅ በቅርቡ ለምረቃ ለማብቃት እየተሰራ መሆኑን ከነሷቸው መካከል ይገኝበታል ።
በግድቡ ዙሪያ ኢዜአ ያነጋገራቸው የቦንጋ እና የጋምቤላ ነዋሪዎች የግድቡ ግንባታ የይቻላል መንፈስ መገለጫችንና በመተባበር የኢትዮጵያን የልማት ህልሞች ሁሉ ማሳካት እንደሚቻል ማሳያ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ወይዘሮ ባርታ ታዬ የቦንጋ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ፤ ግድቡ ለኛ ኢትዮጵያዊን ከድህነት መውጫና እራስን ለመቻል ከሚሰሩ በርካታ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱና ቀዳሚ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያዊያን ሁሉን አቀፍ ተሳትፎና ድጋፍ እየተገነባ ያለ፤ እጅግ የምንኮራበትና ለልጆቻችን የምንናወርሰው ታሪካችን ነው ብለዋል።
ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ በማድረግ አሻራቸውን በማሳረፋቸው ኩራት እንደሚሰማቸው የገለጹት ወይዘሮ ባርታ፣ በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ በመስማታቸው ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል ።
የዚህ ትውልድ አካል በመሆኔ ትልቅ ደስታ ይሰማኛል ያሉት ደግሞ ሌላኛው የቦንጋ ከተማ ነዋሪ አቶ ታሪኩ ታዬ በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ በመግለፃቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል ።
መላው ህዝብ ባለው አቅም ተባብሮ የሚገነባው ግድቡ ከተባበርን የማንችለው ነገር እንደሌለ ያሳየን ትልቅ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
አቶ አስፋው ገዙሙ በበኩላቸው፣ የህዳሴው ግድብ ኢትዮጵያ ያለማንም እርዳታ በራሷ አቅም የምትገነባው የአንድነትና የይቻላል መንፈስ መገለጫችን ነው ሲሉ አብራርተዋል።
በተመሳሳይ ከጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ኡባንግ ፒተር በሰጡት አስተያየት፤ የሁሉም ኢትዮጵያውያን አሻራ ባረፈበት የህዳሴ ግድብ ግንባታ አፈፃፀም ዙሪያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት ማብራሪያ የጠበቁት ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
አሁን ላይ የግድቡ ግንባታ መጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረሱ ለሁሉም ዜጋ ተስፋን የፈነጠቀና ለሌሎች መሰል ፕሮጀክቶች ግንባታ ህዝቡን የሚያነሳሳ መሆኑን ተናግረዋል።
ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ አብዮት አለማየሁ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት በማስመልከት የሰጡት ማብራሪያ የሚያስደስት ነው ብለዋል።
እኛ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ተባብረን ከሰራን የታለሙትን የልማት ህልሞች ሁሉ ማሳካት እንደሚቻል የህዳሴው ግድብ ዋነኛ ማሳያ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የህዳሴ ግድብ ግንባታን ውጤታማነት አስመልክተው የሰጡት ማብራሪያ በእጅጉ የሚያስደስት መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌለው የጋምቤላ ከተማ ነዋሪ አቶ ደፋር ተሬሳ ናቸው ።
ሌላው የጋምቤላ ከተማ ነዋሪ አቶ ዘሪሁን በልሁ ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤት አባላቱ ስለህዳሴ ግድብ ያደረጉት ገለጻ ብዥታን ያጠራና ለሌሎችም ፕሮጀክቶች የሚያዘጋጅ ነው ብለዋል።
በቀጣይ ለሚከናወኑ የልማት ስራዎች ሁሉ መሰረታቸው ሰላም ነውና ለሰላም የተከፈተው በር መቼውንም አይዘጋም በሚል የሰጡት ማብራሪያ በሌሎች ተቀባይነት ሊቸረው የሚገባ ጉዳይ መሆኑንም አንስተዋል።