ቀጥታ፡

ሕዳሴ ግድብ ለአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ውህደት ወሳኝ አቅም ነው- የኢሲኤ ቀጣናዊ ትስስርና የንግድ ክፍል ዳይሬክተር ስቴፈን ካሪንጊ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 13/2017(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቀጣናዊ የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስር በመፍጠር ለአህጉራዊ የኢኮኖሚ ውህደት ወሳኝ አቅም እንደሚፈጥር በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን(ኢሲኤ) ቀጣናዊ ትስስርና የንግድ ክፍል ዳይሬክተር ስቴፈን ካሪንጊ ገለጹ።

ዳይሬክተሩ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል አመንጪ የሆነችው ኢትዮጵያ ለምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጣና ሀገራት የኃይል ትስስር ማዕከል መሆኗን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ለተለያዩ ሀገራት ኃይል እያቀረበች መሆኗን አድንቀው፤ ከኬንያ ጋር በኤሌክትሪክ ኃይል ማስተሳሰር የሚያስችል ግዙፍ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ተሸካሚ መስመር መዘርጋቱንም ገልጸዋል።

ይህም ኢትዮጵያ ለቀጣናው የኃይል መሰረተ ልማት ትስስር እያደረገች ያለውን ሚና የሚያሳይና ከምስራቅ አፍሪካ አልፎ ለደቡብ አፍሪካ ቀጣና ጭምር የኃይል ቋት ሆና እንድታገለግል የሚያደርግ ነው ብለዋል።

የታዳሽ ኤሌክትሪክ ኃይል ልማትም የኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነትን ከማሳደግ ባለፈ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስ የማይተካ ጉልህ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን በማሻሻል የአፍሪካን የኢንዱስትሪ ልማት ለማፋጠን ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

በተለይም የአፍሪካን የንግድና ኢንቨስትመንት ሥርዓት በማሳለጥ ለአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራ የማይተካ ሚና እንደሚጫዎት አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራ አቅም የሚሆኑ ታላላቅ የንግድና ኢንቨስትመንት አስቻይ ሁኔታዎችን እየፈጠረች መሆኗን አብራርተዋል።

ስምምነቱን ለመተግበር ስትራቴጂ በማዘጋጀት የወሰደችው ትልቅ እርምጃ ሌሎች ሀገራት በተሞክሮነት ሊወስዱት የሚገባ ነው ብለዋል።

በልዩ የኢኮኖሚ ዞን ግንባታ፣ በአቪየሽን፣ በትራንስፖርትና ግብርና ዘርፍ የኢንቨስትመንት ፍሰትን በማሳደግ ስምምነቱን ለመተግበር ያላትን ቁርጠኝነት እያሳየች መሆኗን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ስኬትም ከራሷ ዜጎች ፍላጎት ባሻገር በነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነቱ መርህ ለአፍሪካውያን ጭምር ክህሎትና ሃብትን ማቅረብ እንደሚያስችላት አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም