ቀጥታ፡

የባህር በር ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ዘላቂ የብሔራዊ ደህንነትና የዲፕሎማሲ አጀንዳ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 13/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የባህር በር ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ዘላቂ የብሔራዊ ደህንነትና የዲፕሎማሲ አጀንዳ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከትናንት በስቲያ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብር የመልማት ፍላጎቷን በተግባር ስታሳይ መቆየቷን ገልጸዋል።

የባህር በር ጥያቄዋም በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ጦር የሚያማዝዝ ሳይሆን በዲፕሎማሲያዊ ንግግር የሚፈጸም መሆኑን አረጋግጠዋል።

የተለያዩ ሀገራት የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት እንዳለው መመስከራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው አንስተዋል።

የባህር በር ለኢትዮጵያ የትውልዱ ጥያቄና የህልውና ጉዳይ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘብ እንደሚገባም ለምክር ቤቱ በአጽንኦት ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ (ዶ/ር) በዚሁ ጉዳይ ላይ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ባለፉት ሰባት ዓመታት በዲፕሎማሲው መስክ ከፍተኛ ስኬት መመዝገቡን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ትስስርንና የጋራ ልማትን በማፋጠን፣ ብሪክስን በመቀላቀል የባለብዙ ወገንና የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኖዋን በማስፋት እንዲሁም በሀገራዊ የልማት ሥራዎች እመርታ ማምጣቷን አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተከተሉት በሳል የዲፕሎማሲ አካሄድ የሀገራችን ዓለም አቀፍ ተፅዕኖና ተሰሚነት መጨመሩንም ገልጸዋል።

የበለጸጉ ሀገራት ለተከታታይ ትውልድ የሚተርፍ የዲፕሎማሲ አጀንዳ በመቅረፅ ብሔራዊ ጥቅማቸውን ማስከበራቸውን ያወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ኢትዮጵያም ዘላቂ ጥቅሟን ለማረጋገጥ እየሰራች ነው ብለዋል።

የለውጡ መንግሥት የኢትዮጵያን የባህር በር የማግኘት ፍላጎት በይፋ በመግለፅ የትውልዱን የዘመናት ህልም ለማሳካት የጀመረውን ጥረት በዋና ማሳያነት አንስተዋል።

በዲፕሎማሲው መስክ የዓባይ ወንዝ እና የባህር በር የማግኘት ጉዳይ ለኢትዮጵያ ዘላቂ የብሔራዊ ጥቅምና የብሔራዊ ደህንነት ዐቢይ የዲፕሎማሲ አጀንዳ መሆኑን ገልጸዋል።

ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት እና ትውልድ ተሻጋሪ የዲፕሎማሲ ሥራዎች እንዲሳኩ ኢንስቲትዩቱ በጥናትና ምርምር ለማገዝ ስትራቴጂ ቀርጾ እየሰራ ነው ብለዋል።

በቀጣይም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የዲፕሎማሲ የተፅዕኖ አድማስ ከፍ ለማድረግና ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም