የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ በተለያዩ የህክምና ትምህርት ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች እያስመረቀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ በተለያዩ የህክምና ትምህርት ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች እያስመረቀ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 13/2017(ኢዜአ)፦የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ በተለያዩ የህክምና ትምህርት ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች የምረቃ ስነስርዓት እያካሄደ ይገኛል።
በአድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ባለው የምረቃ ስነስርዓት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሃንስ ጫላ፣ የየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ዋና ፕሮቮስት ዶክተር አንተነህ ምትኩን ጨምሮ የተለያዩ የከተማዋ አመራሮች ተገኝተዋል።
ኮሌጁ በተለያዩ የህክምና ትምህርት ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 186 ተማሪዎችን ነው ዛሬ እያስመረቀ የሚገኘው።
በዚሁ ወቅት የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሃንስ ጫላ እንዳሉት ከለውጡ ወዲህ በሽታን ከመከላከል ባለፈ አክሞ ማዳን ላይ ያተኮሩ ውጤታማ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ለከተማዋ ነዋሪዎች ፍትሃዊና ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለመስጠት እየሰራ ሲሆን የጤና ስርዓቱን ዲጂታላይዝ የማድረግ ስራም እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
በቀዳማይ ልጅነት መርሃግብርም በከተማዋ ተምሳሌት የሆነ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የጤና ባለሙያዎች ለጤና ስርዓቱ ወሳኝ መሆናቸውን ጠቅሰው ተመራቂዎች ለከተማዋም ሆነ ለአገሪቱ የጤና ዘርፉግቦች መሳካት ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው አስረድተዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ስር ያለው የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ዋና ፕሮቮስት ዶክተር አንተነህ ምትኩ በበኩላቸው ተቋሙ ከቅድመ ምረቃ እስከ ሰብስፔሻሊቲ ድረስ ያሉ 19 የትምህርት ፕሮግራሞችን እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።
ኮሌጁን በ2030 ወደጤና ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑንና የከተማ አስተዳደሩም ለዚህ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።