በቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ላይ የዳሰሳ ጥናት ሊደረግ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 13/2017 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካ የቀዳማይ ልጅነትልማት ማዕከል ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ እና ዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ ጋር  የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም መነሻ የዳሰሳ ጥናት ለማካሄድ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።

ስምምነቱን የተፈራረሙት የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ከበደ ወርቁ እና የዩኒቨርሲቲዎቹ ፕሬዚዳንቶች ናቸው።

ዶክተር ከበደ የአፍሪካ ቀዳማይ ልጅነት ልማት ማዕከል የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ለመተግበር የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እንዲተገበሩ ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ በመስራት ላይ ያለ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።

የስምምነት  ፊርማው የቀዳማይ ልጅነት የልማት ፕሮግራም የመነሻ ዳሰሳ ጥናት ለማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል።

የአፍሪካ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ማዕከል ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር መሠረት ዘላለም በዘርፉ ለፖሊሲና ስትራቴጂ ምክረ ሀሳብ ለማቅረብ የሚያስችሉ የምርምር ስራዎች እና የባለሙያ የአቅም ግንባታ ተግባራት እንደሚከናወኑ ገልጸዋል።

የዩኒቨርሲቲዎቹ ፕሬዚዳንቶች ለልጆች አስተዳደግ ትኩረት በመስጠት በዘርፉ ላይ በጋራ ለመስራት እና የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት ቁርጠኛ እንደሆኑ መግለጻቸውን ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም