ኢትዮጵያና ኮሪያ ሪፐብሊክ በጤና ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር መስራት ይጠበቅባቸዋል - አምባሳደር ደሴ ዳልኬ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ኮሪያ ሪፐብሊክ በጤና ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር መስራት ይጠበቅባቸዋል - አምባሳደር ደሴ ዳልኬ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 13/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያና ኮሪያ ሪፐብሊክ በጤና ዘርፍ የሚያደርጉትን ትብብር ለማጠናከር መስራት እንደሚገባቸው በኮሪያ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ ገለጹ።
ተቀማጭነታቸውን በኮሪያ ሪፐብሊክ ያደረጉ አምባሳደሮች የዓለም አቀፍ ጤና የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት(Global Health Roundtable with Ambassadors in Korea) ተደርጓል።
በውይይቱ ላይ በኮሪያ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ ተሳትፈዋል።
አምባሳደር ደሴ ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የጤና ሽፋን በማሳደግ፣ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ህክምና በማስፋፋት እና ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎቶችን ለማህበረሰቡ በማቅረብ በዘርፋ ከፍተኛ ለውጥ እያስመዘገበች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የጤና መሠረተ ልማቶቿን ለማስፋፋት ጠንካራ ሥራ እየያከናወነች መሆኑን በማንሳት በኢትዮጵያ በቁልፍ የጤና አመላካቾች መሻሻል መታየቱን ጠቁመዋል።
እንደ ኤች አይቪ/ኤድስ፣ ሳንባ ነቀርሳ እና ወባ ያሉ ተላላፊ በሽታዎች ስርጭት መቀነሱን አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡
በገጠር የጤና አጠባበቅ ተደራሽነት እና የሰለጠኑ የሕክምና ባለሙያዎች ማፍራት ላይ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም ኮሪያ ሪፐብሊክ በኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ(ኮይካ) አማካኝነት ለጤና ዘርፍ ፕሮጀክቶች የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ፣ በህክምና ዘርፍ ስልጠና በመስጠት፣ በዘርፉ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲፈጠር ድጋፍ እያደረገች እንደምትገኝ ተናግረዋል፡፡
በዚህ ረገድም ሁለቱ ሀገራት በጤናው ዘርፍ በተለያዩ ማዕቀፎች ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ማጠናከር እንዳለባቸው አምባሳደሩ መግለጻቸውን በሴኡል የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።