የኢትዮጵያና የአሜሪካ የኢኮኖሚና ኢንቨስትመንት ትብብርን ለማጠናከር ውይይት ተካሔደ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና የአሜሪካ የኢኮኖሚና ኢንቨስትመንት ትብብርን ለማጠናከር ውይይት ተካሔደ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 12/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና አሜሪካ በኢኮኖሚ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላቸውን የሁለትዮሽ ትብብር ማጠናከር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሒዷል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው ከአሜሪካ ሴኔት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ የአፍሪካ ፖሊሲ ከፍተኛ ፕሮፌሽናል ስታፍ አባል ጆን ቶማስዜውስኪን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ውይይቱ የኢትዮጵያ እና አሜሪካን የኢኮኖሚ ትብብር እና አጋርነት ላይ ያተኮረ መሆኑን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ ኢትዮጵያ የአሜሪካ ስትራቴጂካዊ አጋር መሆኗን ገልጸው ሀገራቱ ለረጅም ጊዜ የቆየ እና ጠንካራ አጋርነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ሁለቱ ሀገራት በዓለም ላይ እየተለወጠ የመጣውን የኢኮኖሚ ስርዓተ ምህዳር ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ትብብራቸውን ለማጠናከር የጋራ ቁርጠኝነት እንዳላቸው አመልክተዋል።
የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ የአፍሪካ ፖሊሲ ከፍተኛ ፕሮፌሽናል ስታፍ ጆን ቶማስዜውስኪ የኢትዮጵያ እና አሜሪካ የሁለትዮሽ የኢኮኖሚ ትብብር ለማጠናከር የሚያስችሉ አማራጮችን ለማስፋት ተጨማሪ ውይይቶች እንደሚያስፈልጉ ገልጸዋል።
የጋራ ተጠቃሚነት እና ስትራቴጂካዊ ፋይዳው የጎላ የልማት ትብብር ለሁለቱ ሀገራት ቀጣይ ግንኙነት ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
ሁለቱ ወገኖች የኢትዮጵያ እና አሜሪካን የኢንቨስትመንት እና ንግድ ትብብር ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይም ተነጋግረዋል።
አሜሪካ በኢትዮጵያ ያላትን የኢንቨስትመንት ፍሰት ማሳደግ በውይይቱ አጽንኦት የተሰጠው ጉዳይ ነው።
ስትራቴጂካዊ ትስስር እና ቀጣይነት ያላቸው ውይይቶች የሀገራቱን የኢኮኖሚ እና ኢንቨስትመንት ትብብር ለማጠናከር ወሳኝ እንደሆነም ተመላክቷል።