በመዲናዋ የተጀመረው የምሽት ንግድ ተቋማትና ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ በከተማው ያለው የንግድ እንቅስቃሴ መነቃቃትን የሚያስቀጥል ነው

አዲስ አበባ፤መጋቢት 12/2017(ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረው የምሽት ንግድ ተቋማትና ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ እየታየ የመጣውን የንግድ እንቅስቃሴ መነቃቃት ለማስቀጠል የሚያስችል መሆኑን የአስተዳደሩ ንግድ ቢሮ ገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ የምሽት ንግድ ተቋማትና ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ የሚያሳልጥ ደንብ ቁጥር 185/ 2017 በማውጣት ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።

በተጨማሪም መደበኛ ያልሆነ የጎዳና ላይ ንግድን ስርዓት ለማስያዝ ደንብ ቁጥር 184/ 2017 አውጥቶ ወደ ትግበራ መግባቱ ይታወሳል፡፡

ቢሮው "የዘመነ የንግድ ሥርዓት ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት" በሚል መሪ ሃሳብ በወጡ ደንቦች ዘሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄዷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ ሀቢባ ሲራጅ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ ሁለቱ ደንቦች ከፀደቁበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ ተደርገዋል፡፡

በምሽት የንግድ ተቋማትና ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የወጣው ደንብ ቁጥር 185/ 2017 ከዚህ ቀደም የወጣና ስራ ላይ የነበረው ደንብ ቁጥር 88/2009 ያሻሻለ መሆኑን ጠቁመዋል።

አዲሱ ደንብ አሁን በከተማው እየታየ ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ መነቃቃት ለማስቀጠል የሚያስችል ወቅቱን ያገናዘበ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአፍሪካ መዲና በሆችው አዲስ አበባ ከተማ በምሽት የንግድ ተቋማትና ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ተወዳዳሪነቷን የሚያጠናክር መሆኑን አመልክተዋል።

በከተማው የተገነቡ መሰረተ ልማቶች ገቢ እንዲያመነጩና ነጋዴው ህብረተሰብም ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚያስችልም አመልክተዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተጀመረው የመንግስት ተቋማት የምሽት አገልግሎት አሰጣጥ ውጤት ማስገኘቱን ያስታወሱት ቢሮ ኃላፊዋ፤ ይህን ተሞክሮ የንግድ ተቋማት እንዲወስዱት በማድረግ የስራ ባህልን ለመቀየር እንደሚያስችል ተናግረዋል።

መደበኛ ያልሆነ የጎዳና ላይ ንግድ ስርዓት ለማስያዝ የወጣው ደንብም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የጎዳና ላይ ንግድ እያሳደረ ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያስቀር አመላክተው፤ እነዚህ ነጋዴዎች ወደ ህጋዊ ንግድ ስርዓት እንዲመጡ እንደሚያስችልም ጠቁመዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ አምስት ንግድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መልካሙ ቶላ እንደገለጹት፤ የምሽት ንግድ ተቋማትና ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ደንብ የስራ ባህልን የሚያሳደግ ነው።

ሌላኛው የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት ንግድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ተወካይ አቶ ምትኩ ጎንፋ በበኩላቸው፤ ኢ- መደበኛ የሆኑ ነጋዴዎችን ወደ ንግድ ስርዓት የሚያስገባ፣ ህብረተሰቡም በምሽት የተሳለጠ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስቸል መሆኑን አመልክተዋል።

በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት ንግድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጎበና ደበሳ በበኩላቸው፤ በጎዳና ላይ ንግድን ለማስቀረት የወጣው ደንብ ህገ ወጥ ንግድን የሚያሰቀር ነው ብለዋል ፡፡

የጎዳና ላይ ንግድ ስርዓት ለማስያዝ የወጣው ደንብ ቁጥር 184/ 2017 እና የምሽት ንግድ ተቋማትና ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ደንብ ቁጥር 185/ 2017 የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም ጸድቆ ወደ ትግበራ ገብቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም